
ሐሙስ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. አመሻሽ የኢፌዴሪ መከላከያ የሰሜን ዕዝ መጠቃት፣ በትግራይ ክልል ለተጀመረውና የሰሜን ኢትዮጵያ ክልሎችን ላዳረሰው ደም አፋሳሽ ጦርነት መነሻ ነበር፡፡ ለሁለት ዓመታት በሦስት ዙሮች ሄድ መለስ እያለ ዕልቂቱ ከቀጠለ በኋላ እሑድ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተፈረመው የሰላም ስምምነት የተነሳ ጦርነቱ ቆመ፡፡ ሕወሓት ከፌደራል መንግሥት ጋር ካካሄዱት የአሥር ቀናት ድርድር በኋላ የተፈረመው የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነትን በማስቆሙ፣ በብዙዎች በበጎ የሚነሳ የሰላም ዕርምጃ መሆኑ ብዙ ተብሎለታል፡፡
ይሁን እንጂ ስምምነቱ በትግራይ ክልል ምናልባትም በአፋር ክልል ጭምር የዘለቀውን ጦርነት ማስቆሙን የሚቀበሉ ወገኖችም ቢኖሩም፣ ስምምነቱ በአማራ ክልል አዲስ ዙር ግጭት እንዲፈጠር በር መክፈቱን በማውሳት በሰሜን ኢትዮጵያ የተሟላ ሰላም ያመጣ ነው የሚለውን ለመቀበል እንደሚቸገሩ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ከስምምነቱ ወዲህ በትግራይና በአዋሳኝ ክልሎች ያልተፈቱ ችግሮች መኖራቸውን በመጥቀስ፣ እንዲሁም ከኤርትራ ጋር የተፈጠረውን መቃቃርና ውጥረት መነሻ በማድረግ ስምምነቱ የትግራይን ጦርነት አስቆመ እንጂ በሰሜን ኢትዮጵያ ቀጣና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት አላስቻለም የሚል ቀቢፀ ተስፋ የተሞላው አስተያየት የሚሰጡም አሉ፡፡
ላለፉት ሦስት ዓመታትም ይኸው ቀቢፀ ተስፋ ስምምነቱን ሲከተለው የቆየ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ፕሪቶሪያ በተፈራራሚዎቹ መካከል ዋና መካሰሻና መወዛገቢያ አጀንዳ ወደ መሆን ተሻግሯል፡፡ የፕሪቶሪያ ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መመሥረት ቢቻልምና አንዳንድ የስምምነት አንቀጾችን ለማስተግበር በተለያዩ አጋጣሚዎች ጥረቶች ቢደረጉም፣ ስምምነቱ በተጨባጭ በሥራ ላይ አልዋለም ነው የሚባለው፡፡ ዛሬ የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነትን በመተግበር ጉዳይ ዋና ተፈራራሚዎቹ ሕወሓትና መንግሥት አንዱ ሌላውን ሲከሱ ይደመጣሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ለሦስት ዓመት የቀጠለ ሲሆን፣ ጉዳዩ ተካሮ ሌላ ዙር ጦርነት እንዳይፈጥር ሥጋት ፈጥሯል፡፡
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ሰኞ ጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. የሰሜን ዕዝ ጥቃትን ለማሰብ በተካሄደ መድረክ ላይ ያሰሙት ንግግር፣ በፕሪቶሪያ ስምምነት መተግበር ጉዳይ በመንግሥትና በሕወሓት መካከል ያለው ልዩነት የት ድረስ እንደሄደ የሚጠቁም ነበር፡፡ ‹‹በእኛ ታጋሽነትና ሆደ ሰፊነት እንጂ ሕወሓት ከፕሪቶሪያ በኋላ የሠራቸው ሴራዎችና ያጠፋቸው ጥፋቶች ራሱ ወደ ጦርነት ለመግባት በቂ ምክንያቶች ነበሩ፤›› ብለው ሲናገሩ የተደመጡት ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹሙ፣ ሕወሓት ፕሪቶሪያን የጣሰባቸውን ነጥቦች በመዘርዘር አቅርበዋል፡፡
‹‹ፅምዶ ብሎ ድንበር ሰብሮ ከሻዕቢያ ጋር መተባበርኮ ፀረ ሕገ መንግሥት ሥራ ነው፡፡ እኔን ተሸክሞ ካልገባ በስተቀር ተፈናቃይ እንዲመለስ አልለቅም ማለት እኮ ፀረ ሕገ መንግሥትና ፀረ ፕሪቶሪያ ድርጊት ነው፡፡ ኃይል ማሠልጠን እኮ ፕሪቶሪያ ነው፡፡ ትጥቅ ፈትቶ በመልሶ ማቋቋም (ዲዲአር) መርሐ ግብር የተሰጠው ሠራዊትን ዳግም መመለስ እኮ ፀረ ፕሪቶሪያ ነው፡፡ ለፋኖ ጥይትና ትጥቅ ሰጥተህ አማራ ክልልንም ኢትዮጵያንም እንዲበጠበጥ ማድረግኮ ፀረ ፕሪቶሪያ ነው፡፡ ይህንን ሁሉ እያየን ግን ዳግም ወደ ጦርነት አልገባንም፡፡ አሁን እየሠሩት ያለው ነገር ጉዳት አለው ነገር ግን ወደ ጦርነት መግባቱ የበለጠ ጉዳት አለው፡፡ ተብሎ ነው ዝም የተባለው፡፡ በጊዜ ሒደት ቀልብ የሚገዛ ሰው እየበዛ ይሄድና ቀልብ የሌለው እየተንገዋለለ ይሄዳል በሚል ነው ዝም የሚባለው፤›› በማለት ነው ፊልድ ማርሻሉ ያብራሩት፡፡
ከትግራይ ወገን በተለይም ከሕወሓት በኩል ከጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ስለፕሪቶሪያ ስምምነት በወጣ መግለጫ ግን ዋና አደናቃፊው መንግሥት ነው የሚል ውንጀላ ነው የተሰማው፡፡ የፌዴራል መንግሥት ስምምነቱን ትርጉም አልባና ባለቤት አልባ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ሕወሓት ይከሳል፡፡ ስምምነቱን ተራ ወደ ሆነ የሕወሓት የሕጋዊነት ጥያቄ ጉዳይ እንዲወርድ በማድረግ፣ የስምምነቱን መንፈስ የፌደራል መንግሥቱ አውኮታል ሲልም ይወነጅላል፡፡ የፕሪቶሪያ ስምምነት እንዳይተገበር ከማድረግ አልፎ በትግራይ ላይ ሌላ ዙር ጦርነት ለማወጅ እየተዘጋጀ ነው ሲልም ሕወሓት መንግሥትን ከሷል፡፡ በአጎራባች ክልሎች ትግራይን የሚወጉ ታጣቂዎችን በማደራጀትም መንግሥትን የሚወነጅለው ሕወሓት፣ ለአፍሪካ ኅብረትና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡም ጥሪ አቅርቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባለፈው ሳምንት በፓርላማ በሰጡት ማብራሪያ የፕሪቶሪያን ጉዳይ የጠቀሱ ሲሆን፣ መንግሥታቸው በዚህ ጉዳይ የተከተለውን አቋም አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የወለደችው እያለች ያቀፈችው እናት ነኝ አለች›› የሚል ምሳሌያዊ አነጋገር የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዋነኞቹ የፕሪቶሪያ ስምምነት ከመንግሥት ጋር ተፈራራሚዎች ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ፣ አቶ ጌታቸው ረዳና አቶ አሰፋ አብረሃ የመሳሰሉ ሰዎች ከመንግሥት ጋር መሥራት ቢቀጥሉም በስምምነቱ ወቅት ሚና ያልነበራቸው የሕወሓት ሰዎች ግን የስምምነቱ ዋና ባለቤትና ስምምነቱ አልተፈጸመም ባዮች ሆነው ለመታየት መሞከራቸው ችግር መፍጠሩን ነው የተናገሩት፡፡
From The Reporter Magazine
‹‹በፕሪቶሪያ ሕወሓት ሕጋዊ ምርጫ አላደረገም ይሰርዝ፣ የተመሠረተው መንግሥት ይፍረስ፣ ምክር ቤቱ ይበተን፣ ከሁሉም የተውጣጣ መንግሥት ይመሥረት፣ በሕዝብ የተመረጠ ሕጋዊ መንግሥት በምርጫ ይመሥረት፣ የታጠቀ ትጥቁን አስረክቦ መልሶ ማቋቋም ይደረጋል ነው የተባለው፡፡ የውጭ ግንኙነት፣ የፀጥታና ሰላም የማስፈን ጉዳይ የፌደራል ሥልጣን ነው ይህን እቀበላለሁ ተብሎም ነው ስምምነቱ የተፈረመው፡፡ ይህንን ደግሞ ስምምነቱ ብቻ ሳይሆን፣ የራሱ የሕወሓት ሕገ መንግሥት ራሱ ነው የሚለው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ አግባብን ተከትሎ ችግሮች ይፈታሉ ነው የተባለው፡፡ ሕገ መንግሥቱን አልቀየርነውም፣ እነሱ ሲኖሩ የሚሠራ ሲወርዱ የማይሠራ ሊሆን አይችልም፤›› በማለት ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የአጨቃጫቂ ቦታዎች ጉዳይ አፈታትም ሆነ የተፈናቃዮች አመላለስ ሁኔታ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ዕልባት ለመስጠት የተደረሰውን ስምምነት ሕወሓት እንጂ መንግሥታቸው እንዳልጣሰ በሰፊው አብራርተው ነበር፡፡
አሁን የፕሪቶሪያ ስምምነት ባለቤትና አስተግባሪ ጉዳይ ጭምር መካሰሻ ሲሆን እየታየ ነው የሚሉ አሉ፡፡ በፕሪቶሪያ ከመንግሥት ጋር ስምምነቱን የተፈራረመው ሕወሓት በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ሕጋዊ ሰውነቱን የተነፈገና ከማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ የታገደ መሆኑን በመጠቆም፣ ስምምነቱም ባለቤት አጥቶ የተንሳፈፈ ሆኗል የሚል አስተያየት የሚሰጡ አሉ፡፡ አጨቃጫቂ የወሰን ጉዳዮችን ለመፍታትም ሆነ ወደ ተግባር ያልገቡ የስምምነት ጉዳዮች ዕልባት ለመስጠት፣ የፕሪቶሪያ ስምምነት በሚያዘው መሠረት ፖለቲካዊ ንግግር ማካሄድ የሚቻልበት ዕድል በአሁኑ ወቅት አለመኖሩን የሚናገሩ ብዙ ናቸው፡፡
አንዳንዶች የፕሪቶሪያ ስምምነት ከሞላ ጎደል መፍረሱንና ሊቀደድ ጫፍ መድረሱን እየተናገሩ ባሉበት በዚህ ጊዜ አንጋፋው የትግራይ ፖለቲከኛ አቶ ገብሩ አሥራት በአንድ ወቅት፣ ‹‹ፕሪቶሪያ ትንፋሽ ለመውሰጃና ጊዜ ለመግዣ ብለው ነው ሁለቱ ወገኖች የተፈራረሙት›› በማለት እንደተናገሩት ሁሉ፣ ፕሪቶሪያ ሳይተገበር ያበቃ ወደ መሆን ተቀይሯል የሚል ሐሳብ የሚያንፀባርቁም አሉ፡፡ ይህን መሠረት በማድረግም የጊዜ ጉዳይ እንጂ ወደ ጦርነት እንደገና መገባቱ የማይቀር መሆኑን አንዳንዶች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡
From The Reporter Magazine
ከሰሞኑ በአንዳፍታ ሚዲያ ቀርበው ‹‹ለመንግሥት ቅርብም ባልሆን ሩቅ አይደለሁም›› በሚል ኮርኳሪ ነጥብ በሰሜን ኢትዮጵያ ከሕወሓት እንዲሁም ከኤርትራ ጋር ሊደረግ ስለሚችል ጦርነት ግምታቸውን የሰጡት ታዋቂው የፍልስፍና መምህር ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር)፣ ከሁለቱም ጋር ሊደረግ የሚችል ጦርነት ስለመኖሩ ተናግረዋል፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት አንድ ትልቅ ቦታ ላይ ያለ አንድ ባለሥልጣን ነገረኝ ያሉትን ጉዳይ ማጣቀሻ በማድረግ የተናገሩት ዳኛቸው (ዶ/ር)፣ ‹‹አንድ ለወልቃይት አንድ ለአሰብማ አይቀርም፡፡ በወረቀትና በፊርማ የሚያበቃ ነገር አይኖርም፡፡ አንዳንድ ለሁለቱም ያስፈልጋል፡፡ ዕድለኛ ከሆንን ሁለቱም በአንድ ላይ ይመጡልን ይሆናል ነበር ያለኝ፤›› ሲሉ፣ ከሕወሓትም ሆነ ከሻዕቢያ ጋር ጦርነት የሚደረግበት ጊዜ እየቀረበ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አሁን ከፕሪቶሪያ ስምምነት መደናቀፍ ጋር በተገናኘ ብዙ አሉታዊ ነገሮች ሲባሉ ቢሰማም እንኳ፣ ፕሪቶሪያ ከሰሜን ኢትዮጵያ ባለፈ በመላው ኢትዮጵያም ሆነ በጎረቤት አገሮች ጭምር ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር ለሚደረጉ ጥረቶች መነሻና መስፈንጠሪያ ሊሆን ይችላል የሚለው ግምት በብዙ ወገኖች ዘንድ ቅቡልነት አግኝቶ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ፕሪቶሪያ ከተፈረመና የትግራይ ጦርነት ከቆመ ብዙም ሳይቆይ በአማራ ክልል አዲስ ዓይነት ግጭት ሲያመረቅዝ ነበር የታየው፡፡ መንግሥት የፋኖ ኃይሎችን ትጥቅ ለማስፈታት በጀመረው ዘመቻ የተቆሰቆሰው ግጭት እነሆ ወደ ሦስተኛ ዓመቱ የተሸጋገረ ሲሆን፣ በክልሉ ከባድ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ማስከተሉ እንደቀጠለ ይነገራል፡፡
በፕሪቶሪያ ድርድር ሒደት በአደራዳሪነት የተሳተፉ ወገኖች ስለፕሪቶሪያ መደናቀፍ ያሉት ባይኖርም፣ የአውሮፓ ኅብረት ግን ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ ፕሪቶሪያ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የሰላም ጉዳይ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ንግግር እንደሚጠይቅ ጠቁሟል፡፡
የፕሪቶሪያ ስምምነት ሦስተኛ ዓመት መቆጠርን አስመልክቶ ኅብረቱ ባወጣው መግለጫ፣ የፌደራል መንግሥትና ሕወሓት የፖለቲካ ውይይት እዲጀምሩ አሳስቧል፡፡ ስምምነቱ ትልቅ ዕርምጃ መሆኑን ከፊርማው በኋላ በትግራይ የመጡ ለውጦችን የከለሰው የኅብረቱ መግለጫ፣ የሽግግር ፍትሕና ተፈናቃዮችን መልሶ የማስፈር የመሳሰሉ ወሳኝ ጉዳዮች እንደሚቀሩ ያስታውሳል፡፡ ከመጪው ምርጫ በፊት መንግሥትና ሕወሓት ወደ ፖለቲካ ውይይት መግባት እንደሚኖርባቸው ያሳሰበው ኅብረቱ፣ በአጠቃላይ በመላው ኢትዮጵያ ያሉ ግጭቶችን ለመፍታት መፍትሔው ከሁሉም አካላት ጋር ወደ ፖለቲካ ውይይት መግባት እንደሆነ ነው ያስረዳው፡፡
በትግራይ የጀመረውንና በአንዳንድ ሪፖርቶች እስከ 800 ሺሕ ሕዝብ በመቅጠፍ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ደም አፋሳሽ ውጊያ ሲባል የቆየውን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በፕሪቶሪያ ማስቆም ከተቻለ፣ በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል የተፈጠሩ ግጭቶችንም ሆነ ኢትዮጵያን ከጎረቤት አገሮች ጋር የሚያጋጩ ጉዳዮችንም በቀላሉ በቀጣይ ድርድሮች መፍታት ይቻላል የሚለው ተስፋ በሰፊው ገዥ ሆኖ ነበር የቆየው፡፡
ከአምስት ወራት ቀደም ብሎ በፋና ቴሌቪዥን በጋራ የቀረቡት በመንግሥትና በሕወሓት ወገን ተወክለው የፕሪቶሪያ ዋና ተደራዳሪና ተፈራራሚ የነበሩት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተሩ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ ስለድርድሩ ሒደትና ስለስምምነቱ መንፈስ ከዚያ ቀደም ያልተሰሙ ጉዳዮችን ሲናገሩ ተደምጠው ነበር፡፡
‹‹ከፕሪቶሪያ ቀደም ብሎ ሲሸልስና ሁለት ጊዜ በጂቡቲ ተገናኝተን ተነጋግረን ነበር፡፡ ፕሪቶሪያ ብቻ ሳይሆን ጂቡቲም ባደረግነው ውይይት አደራዳሪዎቹን እስቲ ውጡልን ብለን ለብቻችን ነው ያወራንባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ ልክ እንደ ቤተሰብ ፀብ ኩርፊያ ብቻ ሳይሆን፣ ዘመድ ጥየቃ የሚመስል ግንኙነት ነበረን፡፡ ፕሪቶሪያ ሰፊ አዳራሽ ውስጥ ነበር መጀመሪያ የተቀመጥነው፡፡ እኛ ግን በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ተነስቶ ሰላምታ መለዋወጥና ተቀራርቦ መነጋገር ነበር የመረጥነው፡፡ ከ11 አጀንዳዎች አምስት የሚሆኑትን በሁለት ቀናት ነበር የጨረስነው፡፡ አደራዳሪዎች እስኪገርማቸው ድረስ ተቀራርቦ በግልጽ መነጋገር በመካከላችን ነበር፡፡ ይህ ነገር በመካከላችን ከነበረ ከፕሪቶሪያ ቀድሞ ሒደቱን ማገባደድ ቢቻል፣ ብዙ ሕይወትና ውድመት መታደግ ይቻል ነበር፡፡ ጥቃቅን እንቅፋቶችና ግትር አቋሞች ባይኖሩ ጦርነቱ ሦስት ዙር ሳይቀጥልና ብዙ ጉዳት ሳያደርስ በሰላም መፍታት ይቻል እንደነበር ይሰማኛል፤›› በማለት ሬድዋን (አምባሳደር)፣ ድርድሩ የነበረውን ቀና መንፈስ አስረድተዋል፡፡
ሐሳባቸውን ሲያክሉም፣ ‹‹ሦስተኛው ጦርነት በሕወሓት በኩል የተደረገው ለአከራካሪ ቦታዎች ማስመለስ በሚል ነበር፡፡ ነገር ግን ወደ ድርድሩ ስንገባ ይህን ጉዳይ ሳያነሱት ቀረ፡፡ ትግራይን ከአጎራባች ክልሎች የሚያወዛግቡ ጉዳዮች ሳይነሱ ድርድሩ ወደ መገባደድ ደረሰ፡፡ እነሱ ካላነሱት እኛም አናነሳም ብለን ተነጋግረን ነበር በመንግሥት በኩል የገባነው፡፡ እነሱ ግን በመጨረሻ ጉዳዩ ካልተነሳ መንግሥት ለእኛ ትቶልናል ማለት ነው ብለው አነሱት፡፡ በዚህ ጊዜ እኛም ስለጉዳዩ አቋማችንን አቀረብን፡፡ ጉዳዩ በመጨረሻ አከራካሪ መሆን ሲጀምር በዚህች አንድ ነጥብ የተነሳ የተገባደደው ስምምነት ሊፈርስ ይችላል የሚል ሥጋት አደረብን፡፡ ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጣልቃ ገብተው እንዲሁም ማይክ ሀመር በጎ አስተዋጽኦ አድርጎ ጉዳዩ ዕልባት አገኘ፡፡ እሱን ጉዳይ ሳንጨርስና ስምምነቱን ሳንፈርም ብንመጣ ግን ከዚያ ወዲህ ብዙ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት በተከሰተ ነበር፤›› ሲሉ የተናገሩት ሬድዋን (አምባሳደር)፣ ፕሪቶሪያ በቀና መንፈስ የተካሄደና ዛሬ አልተፈታም የሚባለው የአወዛጋቢ መሬቶች አጀንዳም በሕገ መንግሥቱ መሠረት ይፈታል ተብሎ መግባባት የተደረሰበት መሆኑን በሰፊው አብራርተው ነበር፡፡
አቶ ጌታቸው ረዳም በበኩላቸው፣ ድርድሩ በጥቃቅን ልዩነቶች እንዳይደናቀፍ ከሁለቱም ወገን ብዙ ቀናነት መታየቱን ነበር የተናገሩት፡፡
‹‹ድርድሩን ሊያሰናክሉ የሚችሉ አንዳንድ የዲሲፕሊን ችግሮች ነበሩ፡፡ ጦርነቱ አልቋል፣ በቃ ጨርሰናል፣ በ24 ሰዓት ውስጥ አስረክቡ፣ እጅ እንድትሰጡ የሚል ጭቅጭቅ ነበር፡፡ በሁሉም ወገን ወጥ አቋም ይዞ በመምጣት ረገድ ችግር ነበር፡፡ በስተመጨረሻ ኮንስቲትወንሲውን የሚቀይር ሰው አለ፡፡ የራሱን ሐሳብና አጀንዳ መሰንቀር የሚፈልግ ሰው ነበር፡፡ እኛ ወደ ድርድሩ የገባነው ጥያቄዎቻችንን በግልጽ አስቀምጠን ተኩስ ለማስቆም የሚያስችል ስምምነት ላይ ለመድረስ አቋም ይዘን ነው፡፡ የትግራይ ክልልን ግዛት በሚመለከት ጥያቄ አላነሳም፡፡ ለምንስ አነሳለሁ? ምክንያቱም በሕገ መንግሥቱ የሚታወቅ ቦታ ነው፡፡ የወሰን ጥያቄ ካለ ተኩስ ማቆሙ ከተደረገ በኋላ በሕገ መንግሥቱ የሚመለስ ነው፡፡ ርዕሳችን አልነበረም፣ የእኛ ርዕስ ተኩስ ማስቆም ነው፡፡ በዚያ መካከል እነሱ እኛን ለምን አያነሱትም ብለው ገምተው ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን ከመንግሥት ወገን ድንገት አንድ ሰው ወይም የሆኑ ሰዎች አነሱት፡፡ ይህ ጉዳይ አከራካሪ ነው አሉ፡፡ እኛ ግን አከራካሪ ነው ብለን ስለማናምን ነው ስለዚህ ጉዳይ ያላነሳነው፡፡ ከተነሳም በኋላ ግን አንዳንዱ የሚፈልገው ነገር ተጨባጭነት የሌለው ነበር፡፡ የፌደራል መንግሥቱን በመጠቀም፣ በፌደራል መንግሥቱ ጫና አለኝ የሚለውን ጥያቄ ማግኘት የሚፈልግ አለ፡፡ ይኼ ልንፈጥረው ከምንፈልገው ሰላም አንፃር ምን ያህል መስዋዕትነት እንደሚያስከፍል የሚያጠራጥር ነገር የለውም፡፡ እኛ ያን ጊዜ ረግጠን ነበር የወጣነው፡፡ ይኼ ግዛት አይመለከተኝም ብላችሁ ፈርሙ የሚባል ነገር ሊኖር አይችልም፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገር ሊባል አይችልም፡፡ ነገሩ የፌደራል መንግሥት ኦሪጅናል አቋምም እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ መጨረሻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ጣልቃ ገብተውበት በስምምነቱ ነገሩ የሚያልቅ እንዳልሆነ ተረጋግጦ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ጉዳዩ ይፈታል የሚል አንቀጽ ስምምነቱ ሰፍሮበት የተፈረመው፤›› በማለት ድርድሩ ያለፈበትን ፈታኝ ሒደት አቶ ጌታቸው በሰፊው ገልጸው ነበር፡፡
አላጋው አባቡ (ዶ/ር) የተባሉ የፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካና ግጭት ጥናት ሳይንስ ምሩቅ “Ethiopia`s Pretoria Peace Agreement and the Fate of the ‘Contested’ Areas” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናት፣ የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት አወዛጋቢ የድንበር ጉዳዮች አጀንዳ ጋ ሲደርስ ፈቅ ማለት እንዳቃተው ጠቁመዋል፡፡ በትግራይም ሆነ በፌደራል መንግሥት ወገን ያለው አቋም የሚቀራረብ አለመሆኑ ታች አጨቃጫቂ አካባቢዎች በሚኖረው ማኅበረሰብ ዘንድም ልዩነቱ እንደሚታይ ነው፣ ታች ሕዝቡ ጋ ወርደው በሠሩት ቃለ መጠይቅ መታዘባቸውን አጥኚው የጠቆሙት፡፡
በርካታ ለሚባሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች የአጨቃጫቂ መሬቶች ጉዳይ መጀመሪያ የትግራይ ሉዓላዊ ግዛት ወደ ቀደመ ሁኔታው ከተመለሰ በኋላ የሚፈታ ጉዳይ ሆኖ እንዳገኙት የጠቀሱት አጥኚው፣ ከእነዚሁ ጋር የሚመጣጠን ቁጥር ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ግን በተቃራኒው ተፈናቃዮች ተመልሰው ሕዝበ ውሳኔ ተካሂዶ የመሬት ይገባኛሉ ቅድሚያ መፍትሔ ሊያገኝ ይገባል የሚል አቋም እንዳንፀባረቁላቸው ነው በጥናታቸው የከተቡት፡፡
ከሰሞኑ ይህንኑ የሚመስል ተቃርኖ የሚታይበት አቋም የወልቃይት ጉዳይን በተመለከተ ሲንፀባረቅ የታየ ሲሆን፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አማኑኤል አሰፋ በወልቃይት አካባቢ ዲሞግራፊ የመቀየር ሥራ እየተሠራ ነው በማለት የአማራ ክልልን ሲወቅሱ ተደምጠዋል፡፡ ተፈናቃዮች ሠፍረው በሕዝበ ውሳኔ የወልቃይትም ሆነ የራያ አካባቢ ጉዳይ እንዲፈታ መግባባት ላይ መደረሱን የጠቆሙት አቶ አማኑኤል፣ ሠፋሪና ወራሪ ሲሉ የከሰሷቸው የአማራ ክልል ኃይሎችን ሒደቱን በማደናቀፍ ከሰዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ትግራይን የከዱ ያሏቸው ሰዎችና የፌዴራል መንግሥት እየተባበረ ነው ብለዋል፡፡
ከሪፖርተር ጋር ከሰሞኑ ቃለ መጠይቅ ያደረጉት የወልቃይት አካባቢ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሸተ ደምለው በበኩላቸው ሰላማዊው የትግራይ ሕዝብ ወደቀዬው ተመልሶ እንዲኖር የከለከለው ማንም እንደሌለ የተናገሩ ሲሆን፣ ተፈናቃዮችን ለፖለቲካ ትርፍ ለመጠቀም የሚፈልገውና ወንጀል ሠርቶ የሔደው ኃይል እንቅፋት መፍጠሩን ጠቁመው ነበር፡፡ ሰላም ሚኒስቴርን በማካተት ውይይትና ንግግር እየተደረገ መሆኑን የገለጹት አቶ አሸተ፣ የአካባቢው በጀት መፈቀዱንና በአካባቢው ተፈናቃዮችን መልሶ ለማስፈርና ሕዝበ ውሳኔ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን ምርጫ ለማድረግ ጭምር አስቻይ ሁኔታ መኖሩን ገልጸው ነበር፡፡