
በኢትዮጵያ የኩላሊት ሕሙማን የሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች በጣም ከባድና ውስብስብ ናቸው። በኩላሊት ሕክምና ላይ የሚታዩ ችግሮች የጤና አጠባበቅ ሥርዓቱን የሚያንፀባርቁም ናቸው፡፡ በተለይ ዲያሊሲስና ንቅለ ተከላ ለሚፈልጉ ሕሙማን አገልግሎት ማግኘት ፈታኝ ነው፡፡ መሆኑ ይነገራል። ሥር የሰደደ የኩላሊት መድከም ያለባቸው ታካሚዎች በሳምንት ከሁለት እስከ ሦስት ጊዜ ዲያሊሲስ መውሰድ እንዳለባቸው ይመከራል፡፡ ይሁን ሕክምናው ውድ በመሆኑ፣ ይህም ለአብዛኛው ታካሚ የሚቀመስ አይደለም። ለደም ግፊት፣ ለደም ማነስ፣ ለካልሲየምና ፎስፈረስ መቆጣጠሪያ የሚያስፈልጉ መድኃኒቶች በየጊዜው መወሰድ ያለባቸው ቢሆንም፣ ዋጋቸው ከፍተኛ በመሆኑ ሕሙማን ብዙ ጊዜ ሕክምናቸውን ለማቋረጥ እየተገደዱ ሕይወታቸውን ያጣሉ። የመድኃኒት ዕጦትና ውድነት፣ በቂ የሕክምና አገልግሎት ተቋማትና የሕክምና መሣሪያ እጥረት ችግሮች ዛሬም ያልተፈቱ የኩላሊት ታማሚዎች ፈተናዎች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማኅበር በኩላሊት ሕመም የሚሰቃዩ ወገኖችን ለመርዳት የተቋቋመ ማኅበር ነው፡፡ ማኅበሩን 11 የኩላሊት ታማሚዎች በጋራ የመሠረቱት ሲሆን፣ ከ200 በላይ አባላትን አፍርቷል፡፡ ለኩላሊት ታካሚዎች የመድኃኒት አቅርቦትና ሌሎች እገዛዎችን ከማድረግ አኳያ ምን እየሠራ ነው? የሚለውን የማኅበሩ ሰብሳቢን አቶ ቢኒያም አበራን አበበ ፍቅር አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡– የኢትዮጵያ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማኅበር እንዴት ተመሠረተ?
አቶ ቢንያም፡– ማኅበሩ ከሁለት ዓመት በፊት የተመሠረተ ሲሆን፣ መሥራቾቹም 11 የኩላሊት ሕሙማን ናቸው፡፡ ማኅበሩን ለመመሥረት ያነሳሳን ጉዳይ ዳግሞ የኩላሊት ታማሚዎች ሕክምና ካገኙ በኋላ በየቀኑ የሚወስዱት መድሐኒት እጥረት ለታካሚዎች ፈተና ሆኖ ስላገኘነው ነው፡፡ ይህ መድኃኒት በፍፁም መቋረጥ የለበትም፡፡ ነገር ግን ሰዎች በገንዘብ እጥረትና ከመድኃኒት አቅርቦት ችግር ጋር በተያያዘ መድኃኒት እያቋረጡ ይሞታሉ፡፡ ችግሩን በጋራ ሆነን ብናቀለው በሚል ዕሳቤ ነበር የችግሩ ሰለባዎች ሰብሰብ ብለን ማኅበር መሥርተን ለመሥራት ያሰብነው፡፡
ሪፖርተር፡– መነሻችሁ በራሳችሁ ላይ እየደረሰ ባለችግር እንደመሆኑ ምን ሠራችሁ?
አቶ ቢንያም፡– እውነት ነው ማኅበሩ የተነሳው የችግሩ ሰለባ በሆኑ ሰዎች ነው፡፡ በመሆኑም የአቅም ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ችግሮቹን ለይቶ ለማወቅና ማንም ምን ያስፈልገዋል የሚለውን ለመረዳት አይቸገርም፡፡ ከውጭ አገርም ሆነ አገር ውስጥ ኩላሊታቸውን የተሠሩ ከ500 በላይ ሰዎችን በአባልነት ማሳተፍ ፈልገን ከእነዚህ መካከል 200 የሚሆኑት አባል ሆነዋል፡፡ ማኅበሩ እነዚህ ታማሚዎች የተለያዩ መድኃኒቶችን በወቅቱ እንዲገኙ ያደርጋል፣ ታማሚዎችንም ይጠይቃል፡፡
ሪፖርተር፡– መድኃኒቱን ከየት አግኝታችሁ ነው ድጋፍ የምታደርጉት?
አቶ ቢንያም፡– የመድኃኒት አቅርቦት ሲቆራረጥ ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎትና ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ጋር በመነጋገር ችግራቸውን ለመፍታት ጥረት እናደርጋለን፡፡ የመድኃኒት እጥረት ሲያጋጥም፣ ለእነዚህ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በደብዳቤና በአካል በመገኘትም በመጠየቅ እናገኛለን፡፡
ሪፖርተር፡- የኩላሊት ሕመምን ለመከላከልና ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ተግዳሮት የሚሆነው ምንድነው?
አቶ ቢንያም፡- አንድ የኩላሊት ታማሚ ቀዶ ሕክምና ለማድረግ ሲፈልግ ለእሱ ብቻ አገልግሎት የሚውሉ ዕቃዎች አሉ፡፡ እነዚህ ዕቃዎች በጣም ውድ ናቸው፡፡ የሚመጡትም ከውጭ ነው፡፡ አንዳንዶቹ በለጋሽ ድርጅቶች አማካይነት የሚመጡ በመሆናቸው በበቂ ሁኔታ አይኖሩም፡፡ በሌላ በኩል በቂ የኩላሊት ሕክምና መስጫ ተቋም አለመኖርና የመድኃኒት ዋጋ ውድነት እንዲሁም የግንዛቤ ችግር ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- ችግሩን ለመፍታት ወይም ለማቃለል እንደ ማኅበር ምን እየሠራችሁ ነው?
አቶ ቢንያም፡– የማኅበሩ ዋና ዓላማ የሰዎችን ሕይወት ለማቆየት የቻልነውን ሁሉ ማድረግ ነው፡፡ ታማሚዎች መድኃኒት በሚቸገሩበት ወቅት ያለው ከሌለው በመስጠት ሕይወቱን እንዲቀጥልለት ማድረግ ነው፡፡ በጋራ የምንወያይበት የቴሌግራም ገጽ አለን፡፡ በዚህ የቴሌግራም ገጽ ላይ መድኃኒት ያለው ለሌለው በራሱ ተነሳሽነት ይሰጣል፡፡ በሌላ በኩል መድኃኒቱን በመውሰድ ላይ እንዳሉ ሕይወታቸው ሲያልፍ በቤተሰባቸው በኩል ለሌሎች እንዲሰጡ የምናደርግበት ሁኔታ አለ፡፡ ከዚህ ባሻገር የማኅበሩ አባል የሆኑ ሰዎች ከፍተኛ የሆነ ወጪ ሲጠየቁ ማኅበሩ የቻለውን የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል፡፡
ሪፖርተር፡- ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ምን አስባችኋል?
አቶ ቢንያም፡- እንደ ማኅበር ተጠናክረን ለታካሚዎች የአንድና የሁለት ዓመት ወጪን የምንሸፍንበትን አሠራር መፍጠር ቢቻል ጥሩ ነው የሚል ትልም አለን፡፡ ይህም የሚሆነው የተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶችን በማስተባበር፣ የታካሚዎችን መድኃኒትና የላቦራቶሪ ምርመራ ክፍያዎችን ዝቅተኛና ተመጣጣኝ ከተቻለ ነፃ እንዲሆኑ ማድረግና መድኃኒት ሳይቆራረጥ እንዲደርሳቸው ማስቻል የሚሉት በቀጣይ ለመሥራት ያሰብናቸው ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- እነዚህንና መሰል ሥራዎችን ለማከናወን እንቅፋት ይሆናሉ ብላችሁ ያስቀመጣችሁት ተግዳሮት አለ?
አቶ ቢንያም፡- በአሁኑ ወቅት በጅማሮ ላይ በመሆናችን ጥቃቅን የሚባሉ ነገር ግን ለታማሚዎች ትልቅ የሆኑ ችግሮችን ከማቃለል የዘለሉ ሥራዎችን ልናከናውን አልቻልንም፡፡ ለዚህም በርካታ ችግሮች ቢኖሩም፣ የአቅም ችግር ዋናው ነው፡፡ የአቅም ውስንነት ስላለብን አባላቱ ተሰባስቦ የምንወያይበት እንዴት እንሥራ ብለን ሐሳብ የምንለዋወጥበት በአጠቃላይ ሥራ የምንሠራበት ቢሮ መከራየት አልቻልንም፡፡ ቢሮ ባለመከራየታችን ደግሞ ሥራችንን አይተው ድጋፍ የሚያደርጉ አካላትን ማግኘት አልቻልንም በመሆኑም ብቸኛው የገቢ ምንጫችን ከአባላቱ የሚወጣ ወርሐዊ ክፍያ ነው፡፡ አባላቱም በሕክምና ወጪ ገንዘባቸውን የጨረሱ በመሆናቸው መዋጮው በቂ የሚባል አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚመጡ ታካሚዎች ለሕክምና ከሚያወጡት ወጪ ባሻገር ቀጠሮ ሲሰጣቸው ለአልጋና ለምግብ እንዲሁም ለሌሎች መሰል ተግባራት የሚያወጡት ወጪ ቀላል አይደለም፡፡ ማኅበሩ ተጠናክሮ በዚህ ሕመም የሚሰቃዩ ሰዎች ተገቢውን ሕክምና በወቅቱ እንዲያገኙ ሁሉም ሰው ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ ማስተላለፍ አፈልጋለሁ፡፡