አብዲራህማን መሐመድ አብዱላሂ ወይም በቅፅል ስማቸው አብዲራህማን ኢሮ የሶማሌላንድን ምርጫ አሸንፈዋል፡፡ ሰውየው በቀጣዩ ወር ሶማሌላንድን በፕሬዚዳንትነት የመምራት ሥልጣን ይረከባሉ፡፡ ከወዲሁ ግን ማን ናቸው? በሶማሌላንድ ፖለቲካ ምን ለውጥ ይዘው ይመጣሉ እንዲሁም የእሳቸው ማሸነፍ ተከትሎ ኢትዮጵያ በምትጎራበተው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ላይ ምን ዓይነት ለውጦች ሊከሰቱ ይችላሉ? የሚሉ ጥያቄዎች በሰፊው እያነጋገሩ ናቸው፡፡
ወደ 177 ሺሕ ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያላት የቀድሞ የእንግሊዝ ቀኝ ተገዥ የነበረችው ሶማሌላንድ ወደ ስድስት ሚሊዮን ሕዝብ እንዳላት ይነገራል፡፡ እንደ አገር ዕውቅና ባይሰጣትም በቀጣናው ከሚገኙ አገሮች በተሻለ ሁኔታ የሚመሰገን የምርጫ ዴሞክራሲ የሰፈነባት ስለመሆኑ በሰፊው ይወሳል፡፡
በዘንድሮው ምርጫም ይኸው የሶማሌላንድ ምሥጉን የምርጫ አፈጻጸም የሚደነቅባቸው ምክንያቶች አላጣም፡፡ ወደ 1.2 ሚሊዮን መራጮች የተሳተፉበት የዘንድሮው ምርጫ በመላ አገሪቱ በተዘጋጁ ወደ 2‚000 በሚደርሱ የምርጫ ጣቢያዎች ድምፅ ተሰጥቶበታል፡፡ በዘንድሮው ምርጫ ወደ 28 የሚሆኑ የውጭ የምርጫ ታዛቢዎች ተጋብዘው መካፈላቸው የተለየ ነገር አልነበረም፡፡ ምርጫው ከዚያ ይልቅ በዓይን አሻራ መለያ መራጮች የሚለዩበት አሠራርን ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ያደረገ በመሆኑ በተለየ ሁኔታ የሚጠቀስለት ሆኗል፡፡
እ.ኤ.አ. ከ2012 ጀምሮ በሶማሌላንድ ሕጋዊ ተደርገው የሚታዩትና ዋናውን የምርጫ ፉክክር የተቆጣጠሩት ሦስት ዋና ዋና ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ላለፉት 14 ዓመታት አገሪቱን ያስተዳደረው በፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ የሚመራው ሰላም፣ አንድነትና ልማት ፓርቲ (Peace, Unity and Development Party) የሚባለው በተለምዶ ‹ኩልሚዩ› እየተባለ የሚጠራው ፓርቲ ምርጫውን የማሸነፍ ከፍተኛ ዕድል አለው ሲባል ነበር፡፡ የሙሴ ቢሂ ፓርቲ በተለይም ሶማሌላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የባህር በር በመስጠት በልዋጩ ዕውቅና ለማግኘት የሚረዳ የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረሙ የመመረጥ ዕድሉ እንዳለው ሲነገር ቆይቷል፡፡
ሌላኛው በፌይሰል አሊ ወራቤ የሚመራው ለፍትሕና ለልማት (For Justice and Development) ፓርቲ ሲሆን፣ ዋና የምርጫ ዘመቻውን በፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ላይ አትኩሮ ሲንቀሳቀስ የቆየ ነው፡፡ ፓርቲው በሶማሌላንድ የሕዝቡ መሠረታዊ ችግር ነው የሚለውን የኑሮ ውድነትና የኢኮኖሚ ቀውስ እንደሚፈታ ሲቀሰቀስ ነው የቆየው፡፡
ሦስተኛው ፓርቲ በአብዲራህማን መሐመድ አብዱላሂ (ኢሮ) የሚመራው የዋዳኒ ፓርቲ ነው፡፡ ይህ ፓርቲ በምርጫው ወቅት ከኢኮኖሚና ከፖለቲካ መረጋጋት በተጨማሪ፣ አገሪቱን ለተሻለ የዲፕሎማሲ ስኬት አበቃለሁ ብሎ መንቀሳቀሱ ለተሻለ ድጋፍና ተመራጭነት እንዳበቃው ነው የተነገረው፡፡
የ69 ዓመቱ የዋዳኒ ፓርቲ መሪ አብዲራህማን ኢሮ የማታ ማታ የ64 በመቶ የመራጮች ድምፅ በማግኘት፣ 34 በመቶ ድምፅ ብቻ ያገኙትን ተቀናቃኛቸው የኩልሚዬ ፓርቲውን ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂን በዝረራ ነበር ያሸነፉት፡፡
እ.ኤ.አ. በ1981 ሶማሌላንድ ሳትበታተን በፊት የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ አገልግሎት ውስጥ ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ቀጥሎ ደግሞ በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ሞስኮ ሶማሊያን በአምባሳደርነት ሲያገለግሉ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሶማሊያ ፈራርሳ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ስትገባ ስደተኛ ለመሆን ተገደዱ፡፡
አብዱራህማን ኢሮ እ.ኤ.አ. ከ1996 ጀምሮ ከቤተሰባቸው ጋር በአውሮፓዋ ፊንላንድ መኖር ቀጠሉ፡፡ የፊንላንድ ዜግነት አግኝተው የምክር ቤት ተመራጭ እስከመሆን መድረሳቸውም በሰፊው ይነገራል፡፡ ወደ ሶማሌላንድ ዳግም በመመለስ እ.ኤ.አ. በ2002 የዋዲኒ ፓርቲን የመሠረቱት ኢሮ የሶማሌላንድ ፓርላማ ተመራጭ ከመሆን ባለፈ ለ12 ዓመታት በአፈ ጉባዔነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
በዲፕሎማሲና በዓለም አቀፍ ግንኙነት ያካበቱት ልምዳቸው በሶማሊላንድ ፖለቲካ ተሳትፏቸው ብዙ እንደጠቀማቸው ይነገራል፡፡ ሰውየው ሁሉንም አቻቻይና ሚዛናዊ ግንኙነት መፍጠር ላይ የተሳካላቸው መሆኑ የማታ ማታ በምርጫው አሸናፊ ሆነው ስድስተኛው የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ለመባል እንዳበቃቸው ነው የሚነገረው፡፡ በምርጫ ዴሞክራሲ ፖለቲካዋ በምትወደሰው ሶማሌላንድ በአሳማኝ ብልጫ አሸንፈው ለፕሬዚዳንትነት የበቁት ኢሮ በመጨረሻ ድላቸውን ሲያውጁ ለሁሉም ወገኖች አድናቆትና ምሥጋናቸውን አጋርተዋል፡፡
‹‹በዚህ ምርጫ ሁላችንም ነን ያሸነፍነው፡፡ ከዘጠኝ የአውሮፓ አገሮችና ከአሜሪካ የመጡ ታዛቢዎች ባሉበት ይህን የመሰለ ሰላማዊ ምርጫ በማድረጋችን ሁላችንም አሸንፈናል፤›› በማለት ነው ምርጫው የመላው ሶማሌላንዳዊያን የጋራ ስኬት መሆኑን የተናገሩት፡፡ ይህ በሶማሌላንድ ዙሪያ ለሚገኙ ዴሞክራሲያዊ ምርጫም ሆነ የሥልጣን ሽግግር ለማድረግ ለተቸገሩ አገሮች የሚያቃጭል የደውል ድምፅ ያለው መልዕክት ነው ተብሏል፡፡ የአገርነት ዕውቅና የሌላት ሶማሌላንድ ይህን መሰል ፍትሐዊ ምርጫ ማስተናገዷ ብዙዎችን የአፍሪካ አገሮችን ትዝብት ላይ የሚጥል መሆኑም ይነገራል፡፡
በስድስቱም የሶማሌላንድ ግዛቶች አስተዳደሮች ፍትሐዊ የመንግሥት አስተዳደር መዋቅር በመገንባት የሳሳ ግጭትና ቁርቁዝን ለማስቆም እንደሚሠሩ ኢሮ ቃል ገብተዋል፡፡ የሶማሌላንድን ዕውቅና የማግኘትና ነፃነት የማወጅ ምኞች ለማሳካት እንደሚተጉም ገልጸዋል፡፡ ያለ ውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት የሶማሌላንድን የውስጥ ችግሮች በሶማሌላንዳዊያን ብቻ ለመፍታትና ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር የሚንፀባረቅበት ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓትን ለማፅናት ቁርጠኛ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ከምርጫው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ በሀርጌሳ ለተሰበሰቡ ደጋፊዎቻቸው ንግግር ያደረጉት ኢሮ፣ ‹‹የሶማሌላንድ ሉዓላዊ ግዛት አካላትን ለማጣት ተገደናል፡፡ ሶማሌላንድን አንድ አድርገን ማዋሀድ አለብን፡፡ በምሥራቃዊ የሶማሌላንድ ክፍል በተፈጠረው ጦርነት የወደመው ኢኮኖሚያችንን እንዲያገግም መሥራት ይኖርብናል፤›› በማለት ተናግረው ነበር፡፡ ሰውየው የሚሉት ይሳካላቸው ይሆን ወይ ከሚለው ጥያቄ ጀምሮ የግል ሰብዕናቸው፣ እንዲሁም የሶማሌላንድ ፖለቲካን የከበቡ በርካታ ጉዳዮች መነሳታቸው ቀጥሏል፡፡
ተመራጩ የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት በጣም ዲፕሎማሲያዊ የሆነ የፖለቲካ አቀራረብን የሚከተሉ ሰው መሆናቸውን የሚናገረው ጋዜጠኛ ኢስማኤል ቡርጋቦ፣ ሶማሌላንድን በተመለከቱ ዋና የፖለቲካ አጀንዳዎች ላይ ለዘብ ያለ አቅጣጫን የሚከተሉ ሰው መሆናቸውን ይጠቅሳል፡፡
‹‹በላስአኖድ ግዛት የተፈጠረውን ቀውስ በተመለከተም ሆነ ከሶማሊያ ጋር የገቡበትን ውጥረት እኔ ካላሸነፍኩ ሞቼ እገኛለሁ በሚል ግትር መንገድ የሚሄዱ ሰው አይደሉም፡፡ ሰውየው የድርድር ሐሳብን የሚያስቀድሙ ናቸው፡፡ ነገሮችን ልክ እንደ ሙሴ ቢሂ በማሸነፍና ባለማሸነፍ መነጽር የሚመለከቱ ዓይነት ፖለቲከኛ አይደሉም፤›› በማለት ይገልጻቸዋል፡፡
ያም ቢሆን ግን ተመራጩ ፕሬዚዳንት ውስብስብ የሶማሌላንድ ችግሮች እንደሚጠብቋቸው ጋዜጠኛው ያብራራል፡፡ ‹‹በላስአኖድ ግዛት ያለውን ጦርነትና ቀውስ እንዴት ይፈቱታል የሚለው ጥያቄ መሠረታዊ ነው፡፡ ወደ 300 የሶማሌላንድ ወታደሮች፣ በርካታ ጀነራሎችና የጦር መኮንኖችን ጨምሮ በዚያ ግዛት ተማርከው ይገኛሉ፡፡ በላስአኖድ ግዛት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የዱልባሀንቴ ጎሳ አባላት የራስ ገዝ አስተዳደራቸውንና ነፃነታቸውን ለማስቀጠል ሲሉ ከባድ ዋጋ የተከፈለበት ውጊያ ገጥመዋል፡፡ ይህን ነፃነታቸውን ደግሞ አሳልፈው ይሰጣሉ ብዬ አላምንም፡፡ የሶማሌላንድ ግዛት አካል ሆነው ለመቀጠል ብዙ ቅድመ ሁኔታ የሚያስቀምጡ ይመስለኛል፤›› በማለት፣ አዲሱ ፕሬዚዳንት በላስ አኖድ ያለውን ችግር እልባት ለመስጠት እንደሚቸገሩ ተናግሯል፡፡
ጋዜጠኛው ማብራሪያውን ሲቀጥልም፣ ‹‹ከኢትዮጵያ ጋር የተፈረመውን ዕውቅና በማግኘት የባህር በር የመስጠት የመግባቢያ ስምምነት እንዴት በተግባር ይተረጉሙታል የሚለውም ተጠባቂ ጉዳይ ነው፡፡ ስምምነቱ ለፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ ራስን በራስ የማጥፋት ዓይነት ሆኖ በምርጫ እንዲሸነፉ መንገድ ጠርጓል ይባላል፡፡ ተመራጩ ፕሬዚዳንት ይህን በመረዳት ይመስላል በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ጉዳዩን እንመለከተዋለን የሚል ለስለስ ያለ አስተያየት ነው የሰጡት፡፡ ከዚህ ውጪ ግን የአገርነት ዕውቅና የማግኘት ጉዳይ ሁሉም የሶማሌላንድ ፖለቲከኞች የሚሞቱለትና አጥብቀው የሚሹት ጉዳይ ነው፤›› ብሏል፡፡
በሶማሌላንድ ፖለቲካ ውስጥ አሁን ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎችም ሆነ የኅብረተሰብ ክፍሎች በአንድነት ያስተሳሰረው የአገርነት ዕውቅና የማግኘት ጥያቄ መሆኑን ጋዜጠኛ ኢስማኤል ጠቅሷል፡፡ በሶማሌላንድ ሰፊ ቁጥር ያለው ጎሳ ኢሳቅ መሆኑን የሚጠቁመው ጋዜጠኛው፣ ይሁን እንጂ ያለው የፖለቲካ ክፍፍል ወደ ንዑስ ጎሳና ታችኛው ማኅበረሰብ ድረስ የጠለቀ በመሆኑ ጎሳ እንደ ሌላው ጊዜ አሰባሳቢ የፖለቲካ መሣሪያ መሆኑ እየቀረ እንደመጣ አክሏል፡፡
አሁን በአሜሪካ የዶናልድ ትራምፕ መመረጥ የሶማሌላንድን ዕውቅና የማግኘት ጥረት ያፋጥናል የሚል ተስፋ በሶማሌላንዶች ዘንድ መፈጠሩን የሚገልጸው ጋዜጠኛው፣ ተስፋ ቢኖርም ነገር ግን የዕውቅና ማግኘቱ ሒደት ረጅም መንገድ እንደሚቀረው ጠቁሟል፡፡
‹‹ሶማሌላንድ በመሠረታዊነት እንግሊዝ በሞግዚትነት የምታስተዳድራት ግዛት ነበረች፡፡ ኢሳቅ ጎሳ አብላጫ ቁጥር ይኑረው እንጂ ዱልባሀንቴና ወርሰንጌሌ የመሳሰሉ የዳሮድ ጎሳ ንዑስ ጎሳዎችም ይኖሩበታል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሁለት የዳሮድ ንዑስ ጎሳዎች ወደ ጎን ተብለው የሶማሌላንድ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚም ሆነ ሌሎች ወሳኝ የአስተዳደርና የማኅበራዊ መዋቅሮች በሙሉ በኢሳቅ ጎሳ ፍፁም የበላይነት በቁጥጥር ሥር መውደቃቸው ከፍተኛ ቅሬታን ፈጥሮ ቆይቷል፡፡ ይህ የጎሳ የፖለቲካ ክፍፍል ለዕውቅናና ለአንድነት ፈተና ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ በራሱ በዋናው የኢሳቅ ጎሳ ውስጥም ወደ ንዑስ ጎሳዎች የወረደ የፖለቲካ ክፍፍል አለ፡፡ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ ለምሳሌ ጠንካራ ወይም አምባገነናዊ ፖለቲከኛ ተደርገው ነው የሚታዩት፡፡ የላስአኖድ ግዛት ችግርም ሆነ ከሶማሊያ ጋር የተፈጠረውን ውዝግብ በኃይል መፍታት ነው የሚፈልጉት፡፡ የቀድሞ ወታደርና ኮሎኔል የነበሩት ሙሴ ቢሂ ኃይለኝነት ያጠቃቸዋል ነው የሚባለው፡፡ በኢሳቅ ጎሳ ውስጥም ቢሆን ሙሴ ቢሂ ነው የላስአኖድ ግዛትን ያሳጡን፣ እንዲሁም ከሶማሊያ ጋር ያጣሉን የሚል ውስጣዊ የፖለቲካ ልዩነት ሰፍኗል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ምርጫ በመጣ ቁጥርና የፖለቲካ ድጋፍ ለማግኘት ሲባል ሽማግሌዎችንና የአካባቢ የጎሳ አለቆችን በገንዘብ መደለልም የተለመደ ነው፤›› በማለት የፖለቲካ ልዩነቱ እስከ ታች የወረደ መሆኑን ያብራራው፡፡
ጋዜጠኛ ኢስማኤል ተመራጩ ፕሬዚዳንት አብዲራህማን ኢሮ ለስላሳ ፖለቲከኛ መሆናቸው ሰፊ ድጋፍ በመራጮች አስገኝቶላቸዋል ይላል፡፡ ይህ የሰውየው ልስላሴና ዲፕሎማሲያዊ ተግባቢነት ደግሞ በውጭ ግንኙነት በኩልም ሰፊ ቅቡልነት እንደሚያስገኝላቸው ግምቱን ይገልጻል፡፡
‹‹ሙሴ ቢሂኮ ቋንቋ ጭምር የሚቸገሩ ሰው ነበሩ፡፡ እኚህኛው ግን በመግባባቱ በኩል የተሻሉ ናቸው፡፡ ከምዕራባዊያን አገሮች ጋር፣ ከዓረቡ ዓለምም ሆነ ከሶማሊያ ጋር ተግባብቶ ለመሥራት አይቸገሩም፡፡ በዋናነት ደግሞ ሶማሌላንዶች ከባላንጣቸው ከሶማሊያ መንግሥት ጋር ተዛዝሎ የሚሠራ የውጭ የፖለቲካ ኃይልን አይቀበሉም፡፡ እንደ ግብፅና ኤርትራ ካሉ የሞቃዲሾ አጋር ከሆኑ መንግሥታት ጋር ሶማሌላንዶች ተሻርከው ይሠራሉ ብዬ አልገምትም፡፡ በዚህ የተነሳ ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘም ሆነ በቀጣናዊ ጉዳዮች ሶማሌላንዶቹ ሲያራምዱት የቆየው ፖሊሲ ይለወጣል ብዬ አልገምትም፤›› ሲል ነው ሐሳቡን ያጠቃለለው፡፡