መንግሥት የሎጂስቲክስ ዘርፉን ሙሉ በሙሉ ለውጭ ባለሀብቶች መክፈቱ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ሥጋት እንደሚፈጥር፣ የኢትዮጵያ የዕቃ አስተላላፊዎችና የመርከብ ወኪሎች ማኅበር አስታወቀ፡፡
ማኅበሩ ይህንን ያስታወቀው ኢትዮጵያ ከሦስት ዓመታት በኋላ የሚደረገውን ዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ጉባዔ ለማስተናገድ መመረጧን አስመልክቶ፣ ሐሙስ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ ነው፡፡
መንግሥት በሎጂስቲክስ ዘርፉ 49 በመቶ የውጭ ባለሀብቶች እንዲገቡ ሕግ ያወጣ ቢሆንም፣ በቅርቡ ከተደረገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ወዲህ ግን ዘርፉ ሙሉ ለሙሉ ለውጭ ባለሀብቶች እንዲደሚፈት ማስታወቁ ተገልጿል፡፡
መንግሥት ከአይኤምኤፍ ጋር ባደረገው ስምምነት ዘርፉ እ.ኤ.አ. በ2026 ለውጭ ባለሀብቶች ሙሉ በሙሉ እንደሚፈቅድ ይገልጻል፡፡
ነገር ግን በቅርቡ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፣ ዘርፉ ከዚህ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ለውጭ ባለሀብቶች መከፈቱን ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡
መንግሥት ለውጭ ባለሀብቶች ዕድል ከመስጠቱ በፊት አገር በቀል የሆኑ ባለሀብቶች ራሳቸውን ትንሽ ጊዜ አጠንክረው እስከሚጓዙ ድረስ ዕገዛ እንዲደረግ ጥያቄ ማቅረባቸውን የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት ውብሸት በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በፊት መንግሥት ኢትዮ ቴሌኮምና ባንኮች ራሳቸውን እንዲችሉና እንዲስተካከሉ ካደረገ በኋላ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ማድረጉን፣ የሎጂስቲክስ ዘርፉም ሙሉ ለሙሉ ለውጭ ባለሀብቶች ከሚከፈት ይልቅ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የጎደላቸውን ነገር እንዲያሟሉ ዕድል መስጠት እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡
የሎጂስቲክስ ዘርፉ ሙሉ ለሙሉ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ይሆናል የሚለውን አለመስማታቸውን የገለጹት አቶ ዳዊት፣ ነገር ግን በአገር ውስጥ ማነቆ ሆነው እያስቸገሩ ያሉና ሊስተካከሉ ያልቻሉ ዘርፎች ክፍት ይደረጋሉ የሚለውን መስማታቸውን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ለማዘጋጀት አራት ጊዜ ውድድሮችን ማድረጓንና ሳይሳካ መቅረቱን ጠቅሰው፣ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚነሳው የሰላም ዕጦትና ተፎካካሪ አገሮች የተሻለ የውድድር ሐሳብ ይዘው በመቅረባቸው እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከሦስት ዓመታት በኋላ እ.ኤ.አ. በ2027 የሚደረገውን ዓለም አቀፍ የሎጂስቲክ ጉባዔ ለማስተናገድ መመረጧን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡ ኢትየጵያ ይህንን ጉባዔ ስታስተናግድ የኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ከዓለም አቀፍ የዘርፉ ባለሙያዎች ጋር እንዲገናኙ ዕድል ይከፍታል የተባለ ሲሆን፣ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ማዕከል ለማድረግ የሚደረገው እንቅስቃሴ ጥሩ ዕድል እንደሚሰጥ አክለዋል፡፡
በጉባዔው ሁሉም አባል አገሮች ስለሚሳተፉ ግዙፍ ዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ድርጅቶች ጋር አብረው እንዲሠሩ ዕድል ይሰጣል ተብሏል፡፡
ዓለም አቀፍ የዕቃ አስተላላፊዎች ማኅበር ፌዴሬሽን እ.ኤ.አ. ከ1926 ጀምሮ ጉባዔውን ሲያካሂድ ነበር ያለው ማኅበሩ፣ በዚህ ጉባዔ በተለያዩ የሎጂስቲክስ ኢንዱስትሪውን ዓብይ ጉዳዮች ላይ ምክክር ይደረጋል ብሏል፡፡