ንብ ኢንተርናሽናል ባንክን በዋና ሥራ አስፈጻሚኒት ለአራት ወራት ብቻ አገልግለው ከኃላፊነታቸውን በለቀቁት እመቤት መለሰ (ዶ/ር) ምትክ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ አቶ በላይ ጎርፉን በተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚነት መመደቡ ታወቀ፡፡
የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰሞኑን ባካሄደው ስብሰባ በተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚነት የመደባቸው አቶ በላይ፣ ባንኩን እያገለገሉ ካሉት ሰባት ምክትል ፕሬዚዳንቶች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ በተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ከመመደባቸው አስቀድሞ የባንኩ የስትራቴጂና የትራንስፎርሜሽን ምክትል ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
እንደ ምንጮች ገለጻ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በባንኩ ውስጥ የነበረው ቆይታ በወራት የሚቆጠር በመሆኑና በተሻሻለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት ለተጠባባቂነት የሚጠይቀውን መሥፈርት ሊያሟሉ አይችሉም የሚል አስተያየት እየተሰጠ ቢሆንም ባንኩ ግን የግድ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሰየም ስላለበት አቶ በላይ ተመርጠው ሹመታቸው እንዲፀድቅ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥያቄ አቅርቧል፡፡
በመመርያው መሠረት በተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሚሰየም የሥራ ኃላፊ ማሟላት ከሚጠበቅባቸው መሥፈርቶች መካከል ለአምስት ዓመት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሆንንና በቀጥታ ተጠሪነቱ ለዋና ሥራ አስፈጻሚው ሆኖ ማገልገልም ይጠበቅበታል የሚል ይገኝበታል፡፡
በተጠባባቂነት ሊቆይ የሚችለውም ለስድስት ወራት በመሆኑ ይህ የጊዜ ገደብ ከመጠናቀቁ በፊት በቋሚነት ባንኩን የሚመራ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሰየም ይኖርበታል፡፡
በዚሁ መሠረት ቦርዱ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከመሰየም ጎን ለጎን በቋሚነት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆኖ የሚያገለግል ባለሙያ ለማግኘት እንደገና ወደ ፍለጋ መግባቱም ታውቋል።
ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ገጥሞት የነበረን ችግር ለመቅረፍ አዲስ የተመረጠው ቦርድ ባንኩን ከነበረበት ችግር የሚያወጡ የተለያዩ ዕርምጃዎችን የወሰደ ሲሆን፣ በተለይ የገጠመውን የገንዘብ እጥረት (ሊኪውዲቲ) ችግር መቅረፍ እንደታለ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
ሆኖም ባንኩን ከነበረበት ችግር ያወጣሉ የተባሉት እመቤት (ዶ/ር) ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለመመደብ እንኳ የሚያስችል ጊዜ በማይሰጥ አኳኋን ንብ ባንክን ለቀው በመንግሥት የተሰጣቸውን ሹመት በመቀበል የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ሥራ መጀመራቸው ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ ቀድመው ስለመወሰናቸው የሚያመለክተው መረጃ ከንብ ኢንተርናሽናል ባንክ መልቀቃቸው ሳይሰማ ቀድሞ የተሰማው የመንግሥታዊ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው መሰየማቸው ነበር፡፡
የንብ ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችም ይህንን ድንገተኛ የሥራ መልቀቂያ የሰሙት ባልተጠበቀ ሁኔታ ነው ተብሏል፡፡ ቆየት ብሎም ከጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን መሰየማቸው ሲሰማ ደግሞ የባንኩ ማኅበረሰብ ብዥታ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል፡፡ እመቤት (ዶ/ር) በአጭር ጊዜ ኃላፊነታቸውን የለቀቁበት ምክንያት አሁንም እያነጋገረ ሲሆን ቦርዱ እንደገና አዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወደማፈላለግ እንዲገባ አስገድዶታል፡፡
ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የቀድሞውን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ገነነ ሩጋን በማሰናበትና አዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለመሰየም ባደረገው ምዘና ሦስት ተወዳዳሪዎች ቀርበው እመቤት (ዶ/ር) መመረጣቸው ይታወሳል፡፡
በወቅቱ ከመጨረሻዎቹ ሦስት ዕጩዎች መካከል በተቀመጠው ምዘና ከፍተኛውን ውጤት አምጥተው የነበሩትና ሥራ አስፈጻሚ ይሆናሉ ተብለው በቦርዱ ተመርጠው የነበሩት የቀድሞው የዳሸን ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንትና የቀድሞው የአማራ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ሔኖክ ከበደን ነበር፡፡
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአቶ ሔኖክን ሹመት ሊያፀድቅ ባለመቻሉ በምዘናው ሁለተኛ ውጤት ያስመዘገቡትን እመቤት (ዶ/ር) በቦርዱ እንደተመረጡ ያገኘነው መረጃ ያመለክተል፡፡
ብሔራዊ ባንክ የአቶ ሔኖክን ሹመት ያልተቀበለበትን ምክንያት በመቃወም ግለሰቡ አቤቱታቸውን ካቀረቡ በኋላ ብሔራዊ ባንክ አልቀበልም ያለበትን ምክንደት እንዳነሳ ሪፖርተር ለማወቅ ችሏል። ነገር ግን ክልከላው የተነሳው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ እመቤት (ዶ/ር)ን ከሰየመና ብሔራዊ ባንክም ሹመቱን ካፀደቀ በኋላ በመሆኑ አሽናፊ የሆኑበትን የዋና ሥራ አስፈጻሚነት ቦታ ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡
እንደ ምንጮች ገለጻ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ አዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለመሾም ምናልባት ድጋሚ ያጫቸዋል ተብሎ ከሚጠበቁ መካከል አንዱ ቢሆንም ባንኩ ግን እስካሁን በዚህ ጉዳይ ላይ ውሳኔ እንዳላሳለፈ ለማወቅ ተችሏል።