‹‹ሰው የተሰጠውን ሲያከብር የተሰጠውም ነገር መልሶ እንደሚያከብረው እሙን ነው፡፡ ከበሮውን ተቀበለ አከበረውም፣ ከበሮውም በምላሹ ክብርን ስምን ሰጠው፡፡ ዛሬ ድራምን ስናስብ ዓይናችን ላይ በትልቁ የሚሣለው ተፈሪ ነው፡፡ የእውነት የሚወደድ ማንነት ነበረው ጎደለብን፡፡›› ይህንን ምስክርነት ባለፈው ሳምንት ዜና ዕረፍቱ ከአሜሪካ ለተሰማው ታዋቂው የሙዚቃ ከያኒ ተፈሪ አሰፋ የሰጠው ከያኒው ቸርነት ወልደገብርኤል ሲሳይ ነው፡፡
በድራም አጨዋወቱ የኢትዮጵያን ስም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ያስጠራው ሙዚቀኛ ተፈሪ አሰፋ በከበሮና በሌሎች የሙዚቃ መሣሪያዎች ላይ ምርምር በማድረግና በድንቅ ችሎታው በመጫወት ይታወቃል።
የአገር ሰብ ሙዚቃ ላይ በትኩረት በመሥራቱና ለአያሌ ዓመታት ጃዝ የሙዚቃ ሥልትን በመጫወት ስመጥር የነበረው ተፈሪ፣ በፖላንድ ለሰባት ዓመታት በምት መሣሪያዎች፣ በጃዝ ድራሚንግ፣ በአፍሪካ የተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች የድኅረ ምርቃ ትምህርቱን ማጠናቀቁን ገጸ ታሪኩ ያስረዳል፡፡ በሩሲያ፣ በካዛኪስታን፣ በቤላሩስና በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ከሠራ በኋላ በአሜሪካ ከሌሎች ሙዚቀኞች ጋር ላስታ ሳውንድን በመመሥረት የመጀመሪያ መድረኩን ያሟሸው ከበኩሩ ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ ጋር በመሥራት ሲሆን የላስታ ሳውንድን አልበምንም አበርክቷል። ‹‹Journey to Lasta›› (ጀርኒ ቱ ላስታ) የተሰኘ ዘጋቢ ፊልምም ሌላው ዕውቅና ያገኙበት ነው፡፡ ተፈሪ ከውዳሴ ባንድ ጋር ‹‹ሰላም›› የተሰኘ አልበምንም መሥራቱ ተገልጿል።
በአገር ሰብ ሙዚቃ ላይ አተኩሮ ሲሠራ የቆየው ተፈሪ የኢትዮጵያን ባህላዊ ቅኝቶች ከጃዝ ሙዚቃ ጋር ያዋሃደ ‹‹Origins›› (ኦሪጂንስ) የሚል ስያሜ ያለው የመጀመርያ አልበሙን ያሳተመው ዓምና ነበር፡፡
ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ያስተዋወቀው ታዋቂው ሙዚቀኛ ተፈሪ አሰፋ በኢትዮጵያ ከሙዚቃው መድረክ ባለፈ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤትና በመካኒሳ ሴሚናሪ ጃዝ ትምህርት ቤት በአስተማሪነት ከማገልገሉ በተጨማሪ፣ በነጋሪት ባንድ ውስጥ አገርኛና ዓለም አቀፍ ይዘት ያላቸውን የጃዝ ሙዚቃ በማቅረብ ይታወቅ እንደነበር ገጸ ታሪኩ ያሳያል፡፡
ኢዮኤል መንግሥቱ በሠራው የማ አልበም ላይ ከድራም በተጨማሪ የማሊና የመካከለኛው አፍሪካ ሙዚቃ መሣሪያዎችን በመጫወት ትልቅ አሻራ ማኖሩ ተወስቶለታል።
‹‹የኢትዮጵያን ባህላዊ ዜማዎች ከዘመናዊ ጃዝ ጋር በማዋሃድ፣ ድንበር ዘለል የሆነ ድምፅ ለመፍጠር ሕይወቱን ሰጥቷል፤›› የተባለለት ተፈሪ አሰፋ ማረፉን ተከትሎ የሙዚቀኞቹ ጆርጋና ሙኒት እናት ተዋበች ቢሻው (ዶ/ር) በማኅበራዊ ገጻቸው ላይ ‹‹ተፈሪ ግዙፍ የሙዚቃ ባለሙያ ነበር። ትሁት ደግና የተዋጣለት ሙሉ ሰብእናን የተላበሰ የሚያረጋጋ መንፈስ ያለው ሙሉ ሰው ነበር። ከልጆቼ ከጆርግዬና ሙኒትዬ ለይቼ የማላየው የምወደው የማከብረውና የምሳሳለት የመንፈስ ልጄ ነበር – ሕክምናውን አጠናቆ ይመጣል ነበር እምነቴ፤›› በማለት ሐዘናቸውን ገልጸዋል፡፡
ሙዚቀኛ ተፈሪ ለሕክምና ባቀናበት በአሜሪካ ሎስ አንጀለስ ከተማ በ53 ዓመቱ ያረፈው ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡ ባለትዳርና የልጆች አባት ነበር፡፡