- ‹‹ሕገ መንግሥቱ ወደፊት ይሻሻላል ብሎ ሕግ ማውጣት የሕግ አስተሳሰብ ሳይሆን የፖለቲካ አስተሳሰብ ነው›› የሕግ ምሁራን
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ጥያቄ ተነስቶበት ከፍተኛ ክርክር የተደረገበት የአጠቃላይ ትምህርት ረቂቅ አዋጅ በአብላጫ ድምፅ ፀደቀ፡፡
የፀደቀው የአጠቃላይ ትምህርት አዋጅ ምክር ቤቱ አጠቃላይ ትምህርትን በሕገ መንግሥቱ፣ አገሪቱ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ እንዲሁም በቀረፀችው የትምህርት ሥልጠና ፖሊሲ መሠረት ለሁሉም ዜጎች በፍትሐዊነት ተደራሽ መሆኑን በማረጋገጥ፣ የትምህርት ጥራትን ያመጣል ተብሏል፡፡
ሐሙስ ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም. በተካሄደው 17ኛ መደበኛ ስብሰባ አባላቱ ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን ድንጋጌ መካተቱን በመጥቀስ፣ የምክር ቤት አባላት በረቂቁ ላይ ብርቱ ውይይትና ክርክር ካካሄዱ በኋላ፣ የተቃውሞ ድምፆች ቢሰሙም፣ አዋጅ ቁጥር 1368/2017 ሆኖ በአሥር ድምፀ ተዓቅቦ፣ በሁለት ተቃውሞና በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡፡
ረቂቅ ሕጉ ከወራት በፊት ከሚኒስትሮች ምክር ቤት ወደ ሕግ አውጪው ፓርላማ ሲመራ፣ በረቂቁ አንቀጽ 28 ላይ አንድ ተጨማሪ የአገር ውስጥ ቋንቋ ከፌዴራል የሥራ ቋንቋዎች መካከል፣ የተማሪ ወይም የወላጅ ምርጫን ታሳቢ በማድረግ፣ በየደረጃው ባለው የትምህርት መዋቅር ተወስኖ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ እስከ አሥረኛ ክፍል እንደሚሰጥ ተደንግጎ ነበር፡፡ ረቂቁ ከፌዴራል የሥራ ቋንቋዎች መካከል ቢልም በሕገ መንግሥቱ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ አማርኛ መሆኑን አስቀምጧል፡፡
የአጠቃላይ ትምህርት ረቂቅ በሕግ አውጪው ፓርላማ መሪነት ለወራት ውይይት ሲካሄድበት ከቆየ በኋላ በመደበኛው ስብሰባ እንዲፀድቅ ሲቀርብ ደግሞ፣ በመጀመሪያው ረቂቅ ላይ ከፌዴራል የሥራ ቋንቋዎች መካከል አንድ ተጨማሪ የአገር ውስጥ ቋንቋ ከሚለው ጎን በሕገ መንግሥቱ ሲረጋገጥ የሚፈጸም መሆኑን በማሻሻያ ተደንግጎ ቀርቧል፡፡
ይሁን እንጂ ከምክር ቤት አባላት መካከል በሕገ መንግሥቱ ሳይገለጽ ወደፊት ሕገ መንግሥቱ ሲሻሻል በሚል አዋጅ እንዴት ሊወጣ ይችላል? የሕግ ክፍተት አይደለም ወይ? ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
በፀደቀው አዋጅ አንቀጽ 28 ንፁስ አንቀጽ ሁለት ከፌዴራል የሥራ ቋንቋዎች መካከል አንድ ተጨማሪ የአገር ውስጥ ቋንቋ ለተማሪዎች ይሰጣል ተብሎ መደንገጉ፣ በሕገ መንግሥቱ ከተቀመጠው ድንጋጌ ውጪ መሆኑን የምክር ቤት አባላት አቅርበዋል፡፡
በሕገ መንግሥቱ ስለቋንቋ በሚያብራራው አንቀጽ 5 ላይ የፌዴራሉ መግሥት የሥራ ቋንቋ አማርኛ መሆነ በግልጽ መሥፈሩ አንዱ መከራከሪያ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ኢዜማ አባሉ አቶ ባርጠማ ፈቃዱ በሰጡት አስተያየት፣ ሁለት ወይም ሦስት ቋንቋ በአገሪቱ ቢኖሩ የሚስማሙ መሆናቸው፣ ነገር ግን በሕገ መንግሥቱ አማርኛ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ ስለመሆኑ እንጂ፣ በረቂቁ እንደተደነገገው ቋንቋዎች መኖራቸውን አያመላክትም ብለዋል፡፡ ‹‹ከፌዴራል የሥራ ቋንቋዎች መካከል አንዱ ተጨማሪ ቋንቋ በማለት ሕገ መንግሥት ሲስተካከል ብለን አዋጅ ማውጣት እንችላለን ወይ? ሕገ መንግሥቱ መሻሻል እንዳለበት ሁላችንም እናምናለን፡፡ ነገር ግን ሳናሻሽለው በዚህ መንገድ አዋጅ ማውጣት ይቻላል ወይ?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በተመሳሳይ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የምክር ቤት ተወካይ አበባው ደሳለው (ዶ/ር) በአንቀጽ 28 ላይ ስለቀረበው ድንጋጌ ከሕገ መንግሥቱ ጋር መጋጨት ሲያብራሩ፣ የኢትዮጵያ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ አማርኛ ነው ተብሎ የተቀመጠ ቢሆንም ድንጋጌው ስህተት ያለበት ነው ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 መሠረት ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረን ማንኛውም ሕገ ተፈጻሚነት እንደሌለው መደንገጉን ጠቅሰው፣ ‹‹በዚህ የተነሳ የማይፈጸም ሕግ የምናወጣው ለምንድነው? አዋጆች ሲወጡ አሁን ያለውን የሕዝቦችን ችግር ለመፍታት በመሆኑ፣ ወደፊት የሚተገበር ነገር ግን የአሁኑን ችግር የማይፈታ አዋጅ ለምን መደንገግ አስፈለገ?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በተመሳሳይ አቶ ጋሻው ዳኛው የተባሉ የብልፅግና ፓርቲ የምክር ቤት ተወካይ በበኩላቸው፣ የትኛውም ሕግ የሚመነጨው ከሕገ መንግሥት በመሆኑ ሕገ መንግሥቱን የሚጣረስ መሆን የለበትም ብለዋል፡፡ ‹‹ግልጽ ያልሆነልኝ ነገር ሕገ መንግሥቱ ሲሻሻል ብሎ ሕግ ማውጣት ምን ማለት ነው?›› ሲሉም ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
‹‹ሕገ መንግሥቱ ሲሻሻል ተግባራዊ ይሆናል ብሎ ሕግ ማውጣት ሕገ መንግሥቱ ሲሻሻል ምክር ቤት የለም ወይ? ይህ በምን አግባብ ነው ተግባራዊ የሚደረገው? አንድ ሕግ ሕገ መንግሥቱን የሚፃረር ከሆነ ተግባራዊ አይሆንም ተብሎ ተደንግጐ እያለ፣ ባልተሻሻለ ሕገ መንግሥት ገና ይሻሻላል ብሎ ሕግ ማውጣት የሚቻል ሆኖ አልተሰማኝም፣ ትክክል ነው ብዬም አላስብም፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡
ከሕግ አወጣጥ አንፃር ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ተመራማሪና የሕግ ባለሙያው አቶ ሙሉጌታ አረጋዊ በሰጡት አስተያየት፣ ሕገ መንግሥት ማለት የሕጎች ሁሉ የበላይ መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹መጀመሪያ ሕገ መንግሥቱ እንደሚሻሻል ማንም ሰው እርግጠኛ ባልሆነበትና የሚሻሻልም ከሆነ መቼ እንደሚሻሻል ባልታወቀበት ሁኔታ ይህ ድንጋጌ መቀመጡ አልገባኝም፤›› ብለዋል፡፡
ምክር ቤቱ ሕገ መንግሥቱ ወደፊት ይሻሻላል ብሎ ካሰበ፣ በተሻሻለ ጊዜ የሚፈልገውን አዋጅ ማሻሻል ወይም አዲስ አዋጅ ማውጣት እንጂ፣ ሕገ መንግሥቱ ሲሻሻል ይፈጸማል በሚል ዕሳቤ ዛሬ አዋጅ እንዲያወጣ ሥልጣን እንዳልተሰጠው አስረድተዋል፡፡
‹‹ይህ ትርጉም የሌለው ነው፤›› የሚሉት አቶ ሙሉጌታ፣ ‹‹ይህ ሲሆን ያ ይሆናል ተብሎ የሚቀመጠው በውል ሕግ (Contrat Law) አሠራር ለአብነት ያህል ሰብሉ ከገባ በኋላ፣ ለእኔ ትሸጥልኛለህ ዓይነት ለወደፊቱ ልትዋዋልና ልትፈራረም ትችላለህ፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
‹‹በዚህ መጠን ሕገ መንግሥቱ ሲሻሻል እንዲህ ይሆናል ሲባል አይቼም ሰምቼም አላውቅም፤›› የሚሉት አቶ ሙሉጌታ፣ ‹‹ራሱ ሕግ አውጭው ሥራው ምን እንደሆነ በትክክል ያወቀ አልመሰለኝም፤›› ብለዋል፡፡
ለወደፊቱ ተብሎ ሲቀመጥ እኔ ለዘለዓለም እቆያለሁ ዓይነት ትርጉም ያለው ነው የሚሉት የሕገ ባለሙያው፣ ጉዳዩ የፓርቲ ፕሮግራም ይመስላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የፀደቀው አዋጅ ሕገ መንግሥቱ እስኪሻሻል ተፈጻሚ እንደማይሆን ጠቅሰው፣ ይህ የሕግ አስተሳሰብ ሳይሆን የፖለቲካ አስተሳሰብ ነው ብለዋል፡፡
የአጠቃላይ የትምህርት ረቂቅ አዋጁን ውይይት በበላይነት ሲመራ የቆየው የምክር ቤቱ የሰው ሀብት ልማት ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹አዋጁ የትምህርት አዋጅ እንጂ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ አለመሆኑን እንረዳለን፤›› ብለዋል፡፡
የቋንቋ ጉዳይ በትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲው በግልጽ የተቀመጠ ነው ያሉት ሰብሳቢው፣ የፌዴራል ቋንቋዎች ይሆናሉ ተብለው የተለዩ ቋንቋዎች መኖራቸውን፣ ቋንቋዎቹም ወደፊት በሕገ መንግሥት እንደሚረጋገጡ ተመላክቷል ብለዋል፡፡ ‹‹በሕገ መንግሥቱ ሲረጋገጥ መባሉ፣ ለሕገ መንግሥታችን ክብር መስጠት ግዴታ ስለሆነ ነው፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ሕገ መንግሥቱ ሳይሻሻል እንዲህ ተብሎ መቀመጡ በሚል ለቀረበው ጥያቄ፣ ‹‹ሕገ መንግሥቱ የሚሻሻልባቸው ጉዳዮች ሊኖር ይችላሉ ተብሎ በምክክር ኮሚሽን ይኼው ምክር ቤት በሰጠው ኃላፊነት ብዙ ነገሮች እየተሠሩ ባሉበት፣ ወደፊት ምንም አይመጣም ብሎ ማሰብ የሚያስኬድ አይደለም፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡
‹‹እንደተባለው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 5 አማርኛ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ይሆናል የሚል አለ፣ ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን አማርኛ ብቻ የሚል ነገር የለም፣ ወደፊት ሌሎች ሲጨመሩ የፌዴራል የሥራ ቋንቋዎች ይሆናሉ፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡