በአማኑኤል ብርሃንና በነብዩ ዳንኤል
ሰሞኑን የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የካፒታል ገበያ የቁጥጥር ማጣሪያ መርሐ ግብርን ወደ ሥራ ማስገባቱንና ማመልከቻዎችን መቀበል መጀመሩን ይፋ አድርጓል፡፡ እንዲህ ዓይነት የቁጥጥር ማጣሪያ መርሐ ግብር ወደ ሥራ ሲገባ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ ነው። ይህ መርሐ ግብር አዲስ እንደ መሆኑ መጠን ስለምንነቱ፣ ስለታሪካዊ አመጣጡ፣ ስለይዘቱና ይዞት ስለሚመጣው ጥቅም ገለጻ ማድረግ፣ የሚመለከታቸው አካላት መርሐ ግብሩን ተረድተው እንዲጠቀሙበትና መርሐ ግብሩ የታሰበለትን ግብ እንዲመታ ያስችለዋል።
የዚህን መርሐ ግብር ዋና ሐሳብ በሚገባ ለመረዳት እንዲቻል የጽንሰ ሐሳቡን አመጣጥ ማወቅ ጠቃሚ ነው። ‹‹Sandbox›› የሚለው ቃል የእንግሊዝኛ ቃል ሲሆን፣ የቃሉም የሐሳብ መነሻ የሕፃናት መጫወቻ ዕቃን ያመለክታል። ይህንም ዕቃ በባህር ዳርቻ የሚገኝን አሸዋን በመጠቀም በቁመትና በስፋት አነስ ያሉ ሞዴል ቤቶች ይሠሩበታል። ሕፃናቱም ይህን የአሸዋ ቤት ወይም ሳጥን የተሰኘን ዕቃ በመጠቀማቸው ምናባቸውን ያሰፋሉ፣ አዳዲስ ንድፎችን ይሞክራሉ፣ እንዲሁም የግንባታ ልምድን ያካብታሉ።
የቁጥጥር ማጣርያ መርሕ ግብር፣ ‹የአሸዋ ሳጥን› የሚለውን ቃል ሲወስድ የቃሉም ዓላማ፣ ጥቅምና ይዘት በተመሳሳይ መንገድ በፋይናንስ ሥርዓቱ ውስጥ የሚመጡ አዳዲስ ፈጠራዎች ላይ ለመተግበር በማሰብ ነው። በዚህ አዲስ አሠራር መሠረት አዳዲስ ምርቶችን፣ አገልግሎቶችንና የቢዝነስ ሞዴሎችን ይዘው የሚመጡ ተቋማት ልክ እንደ ሕፃናቱ በተገደበ ጊዜና ቦታ ይዘው የመጧቸውን ምርቶች፣ አገልግሎቶችንና የቢዝነስ ሞዴሎች አነስ ያሉ ሙከራዎችን በገሃዱ ዓለም ውስጥ እንዲሞክሩ ያስችላቸዋል።
ታዲያ ሕፃናት በአሸዋ ሳጥን ሲጫወቱ ምንም እንኳን ምናባቸውን እንዲያሰፉ ዕድልን ቢፈጥርላቸውም፣ የሚሠሯቸው ቤቶች በሳጥኑ ቅርፅና መጠን ይገደባሉ፡፡ በተመሳሳይ መንገስ የፋይናንስ ተቋማት አዳዲስ ሐሳቦችን ሲያመጡ ባለሥልጣኑ በሚያስቀምጣቸው የቁጥጥር ማዕቀፎች ይገደባሉ።
የቁጥጥር ማጣሪያ መርሐ ግብር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሥራ የገባው በዩናይትድ ኪንግደም ኤፍሲኤ በተሰኘው የመንግሥት መሥሪያ ቤት ተነሳሽነት ነበር። እንደ ጽንሰ ሐሳብ እ.ኤ.አ. ከ2014 ጀምሮ ጥናት ሲደረግበት የቆየ ቢሆንም፣ ወደ ሥራ የገባው ግን እ.ኤ.አ. በ2016 ነበር። ወደ ሥራ ከገባበት ጊዜ አንስቶ በዓለም የፋይናንስ መድረክ ላይ ታላቅ ተቀባይነትን አትርፏል። እ.ኤ.አ. ከ2020 ጀምሮ በ57 አገሮች የተለያዩ የቁጥጥር ማጣሪያ መርሐ ግብሮችም ተዘርግተዋል።
ኢትዮጵያ የራሷን የ‹ሳንድ ቦክስ› መርሐ ግብር ለመተግበር ውሳኔ ላይ የደረሰችውም ይህን ዓለም አቀፋዊ የፋይናንስ ነባራዊ ሁኔታን በመመልከት ነው። ይህ ተነሳሽነት ድንገተኛ ከስተት ሳይሆን የአመታት የትብብር ጥረት ውጤት ነው። መርሐ ግብሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንከ ከኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ጋር የሚያስተዳድሩትና በዩኤንዲፒ ድጋፍ ከተቋቋመው የኢኖቬቲቭ ፋይናንስ ላቦራቶሪ ጋር በመተባበር የተመሠረተ ነው። መርሐ ግብሩ ጊዜው ያለፈበት የፋይናንስ አሠራርን ለማስቀረትና የኢትዮጵያን የፋይናንስ ሴክተር ለማዘመን ያሰበ ነው።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ በተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ላይ ማብራሪያ ሲሰጡ ፈጣን፣ ንቁና የዘመነ የፋይናንስ ዘርፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ይህ ሳንድ ቦክስም ይህንን ዕርምጃ የሚያሳካም ነው ማለት ይቻላል።
የቁጥጥር ማጣሪያ መርሐ ግብሩ በፋይናንስ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ተቋማት አዳዲስ ምርቶችን፣ አገልግሎቶችንና የንግድ ሞዴሎችን እንዲሞከሩ ዕድል ይሰጣቸዋል። ታዲያ ይህ ማለት የፋይናንስ ተቋማት አዲስ ነገር ፈጠርን ባሉ ቁጥር ከመንግሥት ፈቃድ ሳያገኙ እንደፈለጉ መንቅሳቀስ ይችላሉ ማለት አይደለም። ይልቁንም የቁጥጥር ማጣሪያ መርሐ ግብሩ አዳዲስ የፋይናንስ አገልግሎቶች፣ ቴክኖሎጂዎችና የንግድ ሞዴሎች ሲመጡ ለተወሰነ ጊዜ የቁጥጥር ደንቦችን በማላላት የተባለውን ምርትና አገልግሎት ወይም የንግድ ሞዴል በውስን ደንበኞች እንዲሞክሩ የሚያስችል ነው።
እስካሁን በነበረው ልምምድ መሠረት በፋይናንስ ዘርፉ የሚመጡ ፈጠራዎችና የአዳዲስ አሠራሮች ትግበራ በመንግሥት የቁጥጥር አቅምና መረዳት የተገደበ ነበር። አንድ ተቋም አዲስ ሐሳብ ይዞ ሲመጣ ይህ ሐሳብ መንግሥት ባለው የቁጥጥር የሕግ ማዕቀፍ የማይታወቅ ከሆነ ሐሳቡ ምንም ያህል ጠቃሚነት ቢኖረውም፣ ይህ ፈጠራ ወደ ሥራ እንዲገባ የሚያስችል አሠራር አልነበረም፡፡ በቁጥጥር ማጣሪያ መርሐ ግብሩ ግን አዳዲስ የፋይናንስ ምርቶች፣ አገልግሎቶችና የንግድ ሞዴሎች በሚመጡበት ጊዜ ሐሳቦቹን ያመጣው አካል ለተወሰነ ጊዜ ከተወሰኑ ከልካይ ሕግጋቶች ነፃ በማድረግ በጥቂት ደንበኞችና በተቆጣጣሪው አካል ክትትልና ድጋፍ አገልግሎቱን በተግባር እየሞከረ ወደ ሥራ እንዲገባ ዕድል ያመቻቻል።
ለምሳሌ አንድ ኢንቨስትመንት ባንክ አዲስ አገልግሎት ይዞ ቢመጣና የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ይህንን አዲስ አገልግሎት የሚቆጣጠር የሕግ ማዕቀፍ ባይኖረው፣ ይህንን አገልግሎት ይዞ የመጣውን ባንክ በደፈናው ‹‹አይቻልም›› ከማለት ይልቅ ተቋሙ አዲስ አገልግሎቱን በባለሥልጣኑ ክትትል እንዲሞክርና ይህንንም ተከትሎ ባለሥልጣኑ አስቻይ መመርያዎችን እንዲያወጣ ያስችላል።
ይህ መርሐ ግብር ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አሉት። ከነዚያ መካከል ለጥቃቅንና አነስተኛ እንዲሁም ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ አቅርቦትን የሚያሳልጡ ቴከኖሎጂዎችን በማዳበር ላይ ይሠራል። እንዲሁም ለኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን አዳዲስ የፋይናንስ ምርቶችንና አገልግሎቶችን ለመፈተሽ ምቹ ሁኔታን ይከፍታል። ከዚህም ባለፈ ለዕለት ተዕለት ነጋዴዎች የኢንቨስትመንት ዕድልን ያስፋፋል፣ የኢንቨስተር ጥበቃን ያጎለብታል፣ እንዲሁም የካፒታል ገበያ መሠረተ ልማትን ያጠናከራል። እንደ አጠቃላይ ደግሞ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውድድርን ለመጨመርና ወጪን ለመቀነስ ያግዛል። ከዚህም አልፎ የፋይናንስ መሣሪያዎችን ተደራሽነትን በማስፋፋት ለአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ ሚና ይኖረዋል።
በዚህ መርሐ ግብር ተቆጣጣሪው የመንግሥት አካል በሚደረጉት ሙከራዎች የሚያገኘውን መረጃ በመጠቀም፣ ማለትም በገሃድ ዓለም ላይ ያለውን እውነታ ባገናዘበ መልኩ ለፈጠራ ተስማሚ፣ እንዲሁም ኢንቨስተሮችን በመጠበቅና ገበያውን በማረጋጋት ላይ ውጤታማ የሆኑ አሠራሮችን ይቀርፅበታል።
የካፒታል ገበያ የቁጥጥር ማጣሪያ መርሐ ግብር የኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥርዓትን አንድ ዕርምጃ ወደፊት ይወስዳል፣ በተጨማሪም ጠንካራ የካፒታል ገበያ ሥርዓትን ለመገንባት ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ለስኬቱም የሁሉም ባለድርሻ አካላት በተለይም የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎችንና የፋይናንስ ተቋማት፣ እንዲሁም የሰፊው የፋይናንስ ሥርዓቱ የነቃ ተሳትፎ ያሻል።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዎቹን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡