የትራንስፖርት ዘርፉን ከማዘመን አንጻር ተሠሩ ብለን ከምንጠቅሳቸው አገልግሎቶች መካከል የሜትር ታክሲ አገልግሎት በዋናነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ልማዳዊ አሠራሮችን አስቀርቷል፡፡ በእነዚህ የሜትር ታክሲዎች የሚጠቀሱ ተገልጋዮች እንደ ቀድሞው በዋጋ አይከራከሩም፡፡ አይጨቃጨቁም ግምታዊ ከሆነ አሠራር ተወጥቶ አገልግሎቱ በኪሎ ሜትርና በሰዓት ተሰልቶ ዋጋ የሚወጣ በመሆኑ አገልግሎቱም ሆነ ተገልጋዩ ለሜትር ታክሲዎች የተዘጋጀው ዲጂታላይዝድ መተግበሪያ ይዳኛቸዋል፡፡ የሜትር ታክሲዎች አገልግሎት መጀመር እያስገኘ ያለው ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ ለመሆኑ በርካታ መገለጫዎች ያሉት ነው፡፡ የትራንስፖርት የአገልግሎት አሰጣጡን ማዘመን ብቻ ሳይሆን ለተገልጋይ ደኅንነትም ቢሆን ይህ ዘመናዊ አገልግሎት ትልቅ ጠቀሜታ ያለው መሆኑ አይታበልም፡፡ ሕጋዊ አሠራርን ከማስረጽ አንፃር ይመዘን ከተባለ እንደ ምሳሌ ሊወሰዱ የሚችሉ አሠራሮችን ለመዘርጋት አስችሏል፡፡
ከሥራ ፈጠራ አንጻርም በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ማስቻሉ በራሱ የሜትር ታክሲ አገልግሎት መጀመር በበጎ የሚታይበት አንድ መለያ ነው፡፡ በዘልማድ ይሠራ የነበረውን የኮንትራት ታክሲ አገልግሎት ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ አስችሏል፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ አገልግሎት ሰጪዎቹ በሚሠሩት ሥራ ልክ ተገቢውን ግብር እንዲከፍሉ የሚያስችል ዕድልንም ፈጥሯል፡፡
‹‹የኮንትራት ታክሲ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ከዚህ ቀደም በቁጥር ግብር ይሰበሰብ የነበረውን የመንግሥት ገቢ አሁን በቴክኖሎጂ በታገዘ መተግበሪያ ተገቢውን ግብር ማሰባሰብ መቻሉም እንደ አገር ትልቅ ዕርምጃ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ስለዚህ የሜትር ታክሲዎች አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋሙ ኩባንያዎች አገልግሎቱን እንዲሰጡ ሲፈቀድ የትራንስፖርት ዘርፉን ከማዘመን ባሻገር መንግሥት እንደ ቀድሞ ለአነስተኛ ታክሲዎች በሚጥለው ግብር ወጥቶ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ግብር ለመሰብሰብ እንደሚቻል ታሳቢ ተደርጎ ነው፡፡
ይሁንና ከሜትር ታክሲዎች አገልግሎት ጋር በተያያዘ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለው አግባብ ያልሆኑ ተግባራት ግን የሜትር ታክሲ አገልግሎት መገለጫ የሆኑ አንዳንድ አሠራሮችን እያበለሻሹት ነው፡፡
ይህም ደንበኞች ወደ ሜትር ታክሲው ኩባንያ በመደወል አገልግሎት ከሚያደርጉት ጥሪ ባሻገር ባሉበት ቦታ ያገኙትን ሜትር ታክሲ ይዘው ሲጓዙ አሽከርካሪዎቹ መተግበሪያዎቹን ለመጠቀም ፈቃደኛ ያለመሆን ጉዳይ ዕርምት ሊወሰድበት ባለመቻሉ እየሰፋ እንዲመጣ ማድረጉ ነው፡፡
ይህም ካልተሳካላቸው ከመተግበሪያዎቹ ውጪ በሞባይሎቻቸው በጫኑት ሕገወጥ የጉዞ መጠን መለኪያዎች አገልግሎቱን እየሰጡ ነው፡፡ በእርግጥ ተገልጋዩ ወደ ሜትር ታክሲዎቹ ስልክ በመደወል መጠቀም የሚችል ቢሆንም አሁን አሁን ተገልጋዩ ካለበት ቦታ እነዚህን ሜትር ታክሲዎች ይዞ የመሄድ ልምድ ከማዳበሩ አንጻር አሽከርካሪዎቹም ይህንን አጋጣሚ ያለአግባብ እንዲጠቀሙበት ዕድል መስጠቱ ግን አይካድም፡፡ ይህ ጉዳይ እንደቀላል መታየት የሌለበትና በቴክኖሎጂ የታገዘ አልግሎቶች ሊያስገኙ የሚችሉበትን ጠቀሜታ በእጅጉ የሚጎዱና ሕገወጥ ሥራዎች እንዲስፋፋ መንገድ የሚከፍት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በሕገወጥ የልኬት መተግበሪያዎች የሚሠራ አገልግሎት የተሳፋሪውን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው፡፡ ብዙዎች ከመተግበሪያ ውጪ ጉዞ ማድረጉ ለተሳፋሪውም ለእነርሱም የሚጠቅም መሆኑን በመግለጽ እያደረጉ ያሉት ሕገወጥ እንዲስፋፋ የሆነበት አንዱ ምክንያት ደግሞ አንዳንድ ተገልጋዮች ተባባሪ ሆነው መገኘት ነውና እንዲህ ያለውን ተግባር ለመቅረፍ ተገልጋዮችም የራሳቸው ኃላፊነት እንዳለባቸው መግለጽ ግድ ነው፡፡
በአጠቃላይ የሜትር ታክሲ ያስፈለገው በአግባቡ በመተግበሪያዎቹ በመጠቀም ለአገልግሎት ለመስጠት በመሆኑ አጋጣሚው ሲገኝ ከመተግበሪያዎቹ ውጪ ተሳፋሪዎች መጫን ሕገወጥ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ስለዚህ ከሜትር ታክሲዎች ጋር በተያያዘ እየተፈጠሩ ያሉ ክፍተቶች በመፈተሽ ከሥር ከሥር ዕርምት እንዲደረግ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ከዚህ ባሻገር በአንዳንድ የከተማው አካባቢዎች በተለይ ጠዋትና ማታ አራት ወይም ስድስት ሰዎችን በመጫን አገልግሎት የሚሰጡ ሜትር ታክሲዎችም ጉዳይ በተያያዘ የሚታይ ነው፡፡ ለምሳሌ አራት ሰዎችን እያንዳንዳቸው 150 ብር በማስከፈል በቋሚነት አገልግሎት የሚሰጥባቸው መስመሮች አሉ፡፡
እንዲህ ያለውን አማራጭ መፍጠራቸው መልካም ቢሆንም አንድ ተጓዥ ለሜትር ታክሲ ቢጓዝ ሊከፍለው ከሚችለው ተመን በላይ ዋጋ እየሆነበት መሆኑ በፍጹም አግባብ አይደለም፡፡ ምክንያቱም አራቱ ተሳፋሪዎች 600 ብር ይከፍላሉ፡፡ ነገር ግን በመተግበሪያዋቹ መጓዝ ቢችሉ ዋጋው ከአራቱም ብር ያነሰ በመሆኑ ያለአግባብ ጥቅም እየተገኘ ነው፡፡ በዚህ ላይ ይህንን ያህል ክፍያ የሚቀበሉት ከመተግበሪያ ውጪ በመሆኑ ግብር የማይከፍሉበት መሆኑን ልብ ሊባል ይገባል፡፡
ሌላም ነገር እንጨምር ደንበኞች የሜትር ታክሲ አገልግሎት ለማግኘት ስልክ ደውለው የሚላክላቸው ታክሲ የታርጋ ቁጥርና በሞባይል ስልካቸው የሚደርሰው የታርጋ ቁጥር የማይመሳሰልበት ሁኔታ የሚፈጥርበት አጋጣሚ አለ፡፡ እንዲህ ያለውን ነገርም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ የሜትር ታክሲዎች መተግበሪያዎችን ይዘው በኮድ 2 ተሽከርካሪ አገልግሎት የሚሰጡስ ሕጋዊ ናቸው? ስለዚህ የሜትር ታክሲዎች አገልግሎት ክፍተቶችን በመጠቀም የሚሠሩ ሕገወጥ ተግባራትን መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡ አስገዳጅ ሁኔታዎችም ሊቀመጥ ይገባል፡፡