ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ሁሉም ባንኮች ባለአክሲዮን የሆኑበት ኢትስዊች አክሲዮን ማኅበር በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ከታክስ በኋላ 789.6 ሚሊዮን ብር አተረፈ፡፡
ኩባንያው የ2016 የሒሳብ ዓመት ሪፖርቱን ባስተዋወቀበት እንዳመለከተው በሒሳብ ዓመቱ ከግብር በፊት ያስመዘገበው ትርፍ በ97 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡
ከሪፖርቱ መረዳት እንደሚቻለው በ2016 የሒሳብ ዓመት ከግብር በፊት ያገኘው ትርፍ ለመጀመርያ ጊዜ የትርፍ ምጣኔውን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማሻገር መቻሉን ነው፡፡ ኢትስዊች በ2015 የሒሳብ ዓመት ከግብር በፊት አግኝቶ የነበረው ትርፉ 534.5 ቢሊዮን ብር ሲሆን ከግብር በኋላ ያገኘው ትርፍ ደግሞ 405.2 ሚሊዮን ብር የነበረ በመሆኑ የ2016 የሒሳብ ዓመት የትርፍ ምጣኔው ወደ እጥፍ የተጠጋ አፈጻጸም የታየበት ስለመሆኑ ያመለክታል፡፡
ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ያገኘው የተጣራ ትርፍ በ2016 የሒሳብ ዓመት ከሁሉም የፋይናንስ ተቋማት በእጅጉ ከፍ ያለ የትርፍ ድርሻ ክፍፍል እንዲሰጥ አስችሎታል፡፡ በዓመታዊ ሪፖርቱ እንደተጠቀሰውም የኢትስዊች አንድ አክሲዮን የሚያገኘው የትርፍ ድርሻ 737.2 ብር ወይም 73.7 በመቶ ነው፡፡
በ2015 የሒሳብ ዓመትም ከፍተኛ የሚባለውን የትርፍ ድርሻ ክፍፍል የሰጠው ኢትስዊች ሲሆን፣ በወቅቱ አንድ አክሲዮን አስገኝቶ የነበረው ትርፍ 719.9 ብር እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ኢትስዊች ይህንን ትርፍ ሊያስመዘግብ የቻለው ዓመታዊ ገቢውን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ በመቻሉ ሲሆን፣ ለዚህም የገቢና የትርፍ ዕድገት የአገሪቱ የዲጂታል ክፍያ አገልግሎት መስፋፋትና የአገልግሎት ክፍያ ዋጋ ከፍ ማለት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
ከኩባንያው ሪፖርት መረዳት እንደሚቻለውም በ2016 የሒሳብ ዓመት ጥቅል ገቢው ለመጀመሪያ ጊዜ 1.13 ቢሊዮን ብር መድረሱ ነው፡፡ በቀዳሚው ዓመት የተመዘገበው ገቢ 606.5 ሚሊዮን ብር በመሆኑ ዓመታዊ ገቢውን በአንድ ዓመት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ማሳደግ ችሏል፡፡
የኦፕሬሽን ሥራን በተመለከተ ኩባንያው ይፋ ባደረገው መረጃ ደግሞ በተጠናቀቀው ዓመት በባንክ ኢንዱስትሪው መካከል በኢትስዊች አማካይነት በአጠቃላይ 123.2 ቢሊዮን ብር የሆነና በድምሩ 94.5 ሚሊዮን እርስ በርስ ተናባቢ የሆነ የኤትኤም አገልግሎት ተከናውኗል፡፡
ይህ ክንውን ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ32 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ያሳያል፡፡ የተናባቢ የፖስ አፈጻጸሙም ከቀዳሚው ዓመት የ125 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ እንደ መረጃው 5.7 ቢሊዮን ብር የሚሆን የተነባቢ ፖስ አፈጻጸም የተመዘገበ ሲሆን፣ ይም 2.1 ሚሊዮን የፖስ ግብይቶች የተከናወኑ መሆናቸውን ነው፡፡
ከገንዘብ ማስተላለፍ ጋር በተያያዘም በሒሳብ ዓመቱ 270.7 ቢሊዮን ብር የሆነና ብዛቱ 49.69 ሚሊዮን ብር ገንዘብ የሚተላለፍ (P2P Transfer) አገልግሎት መስጠቱን ተጠቅሷል፡፡ የገንዘብ ዝውውሩ መጠን ከቀዳሚው ዓመት የ251 በመቶ ዕድገት ያሳየ ሲሆን፣ እንዲህ ያለው የዕድገት ምጣኔ አገልግሎቱ በፍጥነት እያደገና ትልቅ አቅም እየፈጠረ መሆኑን ያመለክታል ተብሏል፡፡
ኢትስዊች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን መረጃ ጠቅሶ እንዳመለከተው በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በሞባይል፣ በኢንተርኔት ባንኪንግና በሞባይል ዋሌት አማካይነት ከ1.11 ቢሊዮን በላይ የገንዘብ ዝውውር ተካሂዷል፡፡ ከዚህ ውስጥ በሞባይል ባንክ አገልግሎት የተዘዋወረው የገንዘብ መጠን 6.71 ትሪሊዮን ብር ነው፡፡ በኢንተርኔት የባንክ አገልግሎትም 15.1 በሚሆኑ የገንዘብ ዝውውሮች (ትራንዝአክሽን) 749.05 ቢሊዮን ብር ተዘዋውሯል፡፡
በሞባይል ዋሌት በኩል ደግሞ በ764.8 ሚሊዮን ትራንዝአክሽኖች 1.02 ቲሊዮን ብር ማዘዋወር መቻሉን ይጠቅሳል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያሳየው በተጠናቀቀው ሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ የሁሉም ባንኮች የኤትኤም ማሽኖች ቁጥር ወደ 14,030 ደርሷል፡፡ በ2015 መጨረሻ ላይ የነበሩት የኤትኤ ማሽኖች ቁጥር 12,016 ነበር፡፡
በተመሳሳይ የፖስ ማሽኖች ቁጥርም ከ7,858 ወደ 10,551 ከፍ ብሏል፡፡ የነዚህ ማሽኖች ቁጥር መጨመር ለኢትስዊች አገልግሎት መስፋፋት አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ይታመናል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክርል ገዥና የኢትስዊች ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ሰለሞን ደስታ እንደገለጹት በፍጥነት እያደገ በሚገኘው የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት አቅርቦት ላይ ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ብቁና ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት በሚችለው ደረጃ ተጨማሪ ፕሮጀክቶችን በመተግበር ላይ ነው፡፡
የካፒታል አቅሙን ለማሳደግም በሒሳብ ዓመቱ አክሲዮችን ለሽያጭ ማቅረቡን ያስታወሱት አቶ ሰለሞን ይህም የኩባንያውን ካፒታል ወደ 1.78 ቢሊዮን ብር ማሳደግ መቻሉንም አክለዋል፡፡
ኩባንያው እየሰጣቸው ያሉ ተጨማሪ አገልግሎቶችን በተመለከተ በኢትዮጵያ ደረጃዎች ባለሥልጣን የፀደቀውን የኢትዮፔይ Dual Interface/Contactless የክፍያ ካርድ ዘዴን ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ማድረጉን ጠቅሷል፡፡ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመትም ተናባቢ የQR Code የዲጂታል ከፍያ (interoperable QR standardization) በተመለከተም ኢትስዊች የትግበራ ሐሳብ በማመንጨት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር በጋራ ሲሠራ መቆየቱንና ይህም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አማካይነት በኢትዮጵያ የዲጂታል ፔይመንት ኮንፈረንስ ላይ በደማቅ ሁኔታ ይፋ የተደረገው በዚሁ ሒሳብ ዓመት መሆኑ አስታውሷል፡፡
ሁሉም የክፍያ አገልግሎት አቅራቢዎች በትግበራ ላይ የሚገኙትን የዲጂታል የክፍያ አማራጮችን ለመጠቀም አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅትና ቅድመ ሁኔታ በማጠናቀቅ እንዲቀላቀሉ መተላለፉንም አመላክቷል፡፡
ኢትስዊች ኢ.ማ. ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ በሁሉም የግልና የመንግሥት በንኮች እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ የተቋቋመ ነው፡፡ በቅርቡም የአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት፣ የክፍያ ሥርዓት ኦፕተሮችና የክፍያ መፈጸሚያ ሰነድ አውጪዎች በባለቤትነት እየተቀላቀሉት ይገኛሉ፡፡ እንደ ዋነኛ ዓላማ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ያለው በፋይናንስ ተቋማት መካከል በዲጂታል አማካይነት የሚደረጉ ግብይቶችን (ክፍያዎችን) ተናባቢ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ የአገር ውስጥ የክፍያ ሥርዓትን ማቅረብ፣ የብሔራዊ ክፍያ ጌትዌይ አገልግሎትን መስጠት፣ ለዲጂታል ክፍያዎች የመጨረሻ ሒሳብ የማጣራትና የማወራረድ የማዕከላዊ አገልግሎት መስጠትና ለፋይናንስ ተቋማት የጋራ መሠረተ ልማትና ሲስተሞች ማቅረብ የሚሉ ይገኙባቸዋል፡፡