በትግራይ ክልል የሚገኙ ሠራተኞች በጦርነቱ ወቅት ያልተከፈላቸውን የ16 ወራት ደመወዝ እንዲከፈላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ባወጣው ደንብ እንደታገደባቸው የክልሉ ሠራተኞች ማኅበር ተወካይ ገለጹ፡
የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ሰሞኑን ባካሄደው መደበኛ ጉባዔ ላይ የትግራይ ክልልን ሠራተኞች በመወከል የተገኙት የማኅበሩ ተሳታፊዎች፣ በዚህ ምክንያት በክልሉ የሚገኙ ሠራተኞች በከፍተኛ ችግር ላይ ስለመሆናቸውም ገልጸዋል፡፡
በተለይ በጦርነቱ ወቅት ያልተከፈላቸውን የ16 ወራት ደመወዝ እንዲከፈላቸው ያደረጉት ጥረት፣ የጦርነቱን ወቅትን ታሳቢ ያደረገ የደመወዝ ክፍያ አይፈጸምም በመባሉ፣ ኮንፌዴሬሽኑ እዲያገላልግላቸው ጠይቀዋል፡፡
በጦርነት ወቅት ያልተከፈላቸው ደመወዝ እንዲከፈላቸው ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ የተደረገባቸው፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ባወጣው ‹‹ደንብ አራት›› ተብሎ በሚጠራ ውሳኔ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
ይህ ደንብ አንድ ሠራተኛ ስለምንም ነገር እንዳይጠይቅ ጭምር ድንጋጌ ያካተተ በመሆኑ፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርን በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም መጠየቅ አትችሉም ብሎ ጥያቄያቸው ውድቅ መደረጉን ለጉባዔያተኛው አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር አሁንም በክልሉ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን በማመልከትም፣ በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ ይሠሩ የነበሩ ሠራተኞች በአሁኑ ወቅት በመጠለያና በተለያዩ ቦታዎች ሆነው ዕርዳታ ጠባቂ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሰው ዛሬ ከቸገረው ነገ ሊያገኝ ይችላል›› ያሉት ተወካዩ፣ ሥራ ላይ በነበረ ሰዓት አገሩን በመርዳት እንደ ኢሰማኮ ላሉ ተቋማትም ተገቢውን መዋጮ ያወጣ የነበረ በትግራይ ውስጥ ያለ ሠራተኛ፣ ዛሬ ችግር ውስጥ በመውደቁና እየሞተም ጭምር በመሆኑ ኢሰማኮና አቻ ማኅበራት ድጋፍ ያደርጉለት ዘንድም ጠይቀዋል፡፡
በሠራተኛው ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በመረዳት ከዚህ ቀደም ኢሰማኮ ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ተወካዩ፣ አሁንም ድጋፍ የሚሹ መሆኑን በመግለጽ ጥያቄያቸውን ‹‹እዚህ ያለው የኢትዮጵያ ሠራተኞች የትግራይ ሠራተኞችን እንድታግዙ ቆሜ እጠይቃችኋለሁ፤›› በማለት ተማፅነዋል፡፡
የትራንስ ኢትዮጵያ ሠራተኛ መሆናቸውን የገለጹት ተወካዩ፣ በክልሉ ብዙ ወደ ሥራ ያልገቡ ድርጅቶች መኖራቸው ለችግሩ መባባስ ምክንያት መሆኑንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ እሳቸው የሚሠሩበት ትራንስ ኢትዮጵያ በአንፃራዊነት ወደ ሥራ መግባቱን ጠቅሰው፣ ከጦርነቱ በፊት ከነበሩት 580 ተሽከርካሪዎች 200 ተሽከርካሪዎች ይዘው ሥራ መጀመራቸውንም ተናግረዋል፡፡
የትግራይ ሠራተኞች ማኅበር ተወካይን አስተያየትና ጥያቄ ተከትሎ የኢሰማኮ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፣ የክልሉ ሠራተኞችን የደመወዝ ጥያቄ ይዘው እስከ ክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ድረስ በመሄድ የተነጋገሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በጉዳዩ ላይም ከሚመለከታቸው ጋር ውይይት ማድረጋቸውንም አስታውሰዋል፡፡
ከውይይቱ በኋላም በደብዳቤ ጭምር ስለጉዳዩ በማሳወቅ ችግሩን ሊፈታ ይችላል የተባለ ከአሠሪ፣ ከማኅበራትና ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት የተወጣጣ ኮሚቴ ተዋቅሮ ጥናት የተደረገበት ጉዳይ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ሁኔታ ያመቻቸው ኢሰማኮ ቢሆንም፣ ጥያቄው አዎንታዊ ምላሽ ሊያገኝ ያለመቻሉን ለጉባዔው አባላት ገልጸዋል፡፡ ለዚህም እንደ ዋና ምክንያት የጠቀሱት በጦርነት ወቅት የሚጠየቅ ደመወዝ መክፈል የማይቻል ስለመሆኑ፣ በሕግ የተቀመጠ ድንጋጌ በመኖሩ ነው፡፡ ይህም ድንጋጌ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ውስጥ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
‹‹ጦርነት እንዲህ ያለውን ነገር ነው የሚያስከትለው፡፡ እንኳን መብት ልትጠይቅ ለሕይወትም የሚያሠጋ ነገር ነው፤›› በማለት ምላሻቸውን የቀጠሉት አቶ ካሳሁን፣ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የወጣው ደንብ አራትም ከዚሁ ጋር የተያያዘ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
ኢሰማኮም የሠራተኞቹን ጥያቄ ለማስመለስ የኢትዮጵያ አሠሪና ሠራተኛ ውስጥ የተካተተ ድንጋጌ እንደገደባቸውም አመልክተዋል፡፡ በዚህ አዋጅ ውስጥ ሥራ ባልተሠራበት ወቅት ደመወዝ መጠየቅ የማይቻልና በጦርነቱ ወቅት የነበረን ደመወዝ ለማስከፈል ፍርድ ቤት ቢኬድ ‹‹ይህ እኛን አይመለከተንም፡፡ ጦርነቱን ያስነሳው እከሌ ነው፡፡ ጦርነቱን ያስነሳው እከሌ ስለሆነ ካሳ መክፈል አለበት የሚሉ አሉ፤›› ያሉት አቶ ካሳሁን እንደዚህ ያሉ ጥያቄዎችን ይዘው ለመጡትም በየትኛው ሕግ ጥያቄያቸውን ለማሰማት አለመቻላቸውንም ተናግረዋል፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ያለውን ክፍተት በመጠቀም እየሠሩ መሆኑን በመግለጽም፣ ለምሳሌ በአዲስ መድኃኒት ፋብሪካ ውስጥ በነበረ የማኔጅመንት ችግር 119 ሠራተኞች ለገጠማቸው ችግር፣ በራሳቸው ተደራጅተው ለመከራከር ገንዘብ በመላክ ጠበቃ ገዝተንላቸው ባደረጉ ክርክር መፍትሔ እንዲያገኙ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡ በትግራይ ክልል በሁለቱ ዓመት የጦርነት ወቅት ላልተከፈለ ደመወዝን የሚጠየቅበት የሕግ አግባብ ባለመኖሩ ክፍተቱ መፈጠሩን አስረድተዋል፡፡
አቶ ካሳሁን በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ያሉትን ጉዳዮች ግን በሕግ መጠየቅ የምንችልበት ሁኔታዎች ስላለ መጠየቅ የሚችሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የጦርነቱ ወቅት ግን በአስገዳጅ ሁኔታ ሥራ ባልተሠራበት ጊዜ ደመወዝ ይከፈል ለማለት ያለው ሕግ ቢገድባቸውም፣ ግን በድርድር ደመወዙ የሚከፈልበት ሁኔታ አሁንም ዝግ አለመሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ከኢፈርት ኩባንያዎች ውስጥ አንዳንዶቹ የደመወዝ ክፍያ መፈጸማቸውን በማስታወስም፣ ይህ የሆነው በተደረገ ድርድር ጭምር በመሆኑ አሁንም በድርድር ያልተከፈለው ደመወዝ እንዲከፈል ጥረት የሚደረግ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡
የትግራይ ሠራተኞች ድጋፍን በተመለከተ በሰጡት ምላሽ ደግሞ፣ ኢሰማኮ ባለው አቅም ድጋፍ ያደረገ ቢሆንም፣ በመጠለያ ያሉትን በሙሉ መደገፍ ከባድ እንደሚሆንባቸው በመጥቀስ፣ የአቅማቸውን እያረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ አቅም ያላቸው ማኅበራት ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡
በዕለቱ ከትራንስፖርት ዘርፉ የተወከሉ የማኅበር መሪዎችም አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖብናል ብለው ያቀረቡት ጥያቄ ነበር፡፡ ይህም የከባድ ተሽከርካሪ ሾፌሮች ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እንደ ተወካዮቹ ገለጻ በአሁኑ ወቅት የአሽከርካሪዎች ትልቅ ተግዳሮት እየሆነ የመጣው ጉዳይ በሰላም ዕጦት ለዘራፊዎች ተጋላጭ መሆናቸው ነው፡፡ ሥራቸውን በሥጋት ጭምር እየሠሩ ሲሆን፣ በአንዳንድ አካባቢዎች እየተደበደቡና እየተዘረፉ ነው፡፡ ይህንን የሚከላከልላቸው ባመኖሩ ችግሩ ተደጋግሞ የተከሰተ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ በመሆኑም ይህ ጉዳይ ጊዜ የማይሰጥና አገልግሎታቸውን ያለ ሥጋት እንዲሰጡ ዋስትና ያስፈልጋቸዋል፡፡
በዚሁ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ አስተያየት የሰጡት ሌላው የሠራተኛ ተወካይ በበኩላቸው፣ በተለይ ከጂቡቲ አዲስ አበባ መስመር ላይ ባሉ ትናንሽ ከተሞች የኮቴ ተብሎ የሚጠየቀው ክፍያ፣ በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ትልቅ ጫና እየፈጠረባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በየኬላው ከ35 እስከ 40 ሺሕ ብር የኮቴ የሚጠየቅ በመሆኑና ካልከፈሉ ደግሞ ሾፌሮቹ ከፍተኛ የሆነ መጉላላት እየደረሰባቸው መሆኑን ሪፖርት እየደረሳቸው በመሆኑ፣ ኢሰማኮ በዚህ ላይ አቋም ወስዶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሔ እንዲፈልግላቸው ጠይቀዋል፡፡
በትራንስፖርት ዘርፍ ሌላው እየታየ ነው ተብሎ በተወካዮቹ የቀረበው አስተያየት፣ ከባድ ተሽከርካሪዎች የመጫን አቅም እንዲቀንስ ከመደረጉ ጋር ተያይዞ እየተፈጠረ ነው ያሉት ችግር ነው፡፡ ይህ አዲስ ሕግ ነው መባላቸውን የጠቀሱት አስተያየት ሰጪው፣ ከወቅታዊው የዋጋ መናርና ካለው የመለዋወጫ ዕቃዎች ዋጋ ጭማሪ አንፃር የጭነት አቅም እንዲቀንስ መደረጉ ድርጅቶችን ለኪሳራ ስለሚዳርግ ይህም ጉዳይ እንዲታይላቸው ጠይቀዋል፡፡ እንደ ትራንስፖርት ዘርፍ ሠራተኞቹ ገለጻ ከሆነ፣ ከዚህ ቀደም 400 ኩንታል ይጭኑ የነበሩ ተሽከርካሪዎች አሁን 350 እና ከዚያ በታች እንዲጭኑ እየተገደዱ በመሆኑ፣ ይህ ልዩነት ገቢያቸው ላይ ጫና እየፈጠረ ነው፡፡
በዕለቱ መደበኛ ጉባዔ መንግሥት በአስቸኳይ ሊመልስ ይገባዋል ተብለው በዋናነት ከተገለጹት ‹‹የደመወዝ ግብር ይቀንስ›› የሚለው ጉዳይ በቀዳሚነት ተቀምጧል፡፡ ከዚህም ሌላ ሠርቶ የመኖር መብትን እየተጋፋ ያለው የሰላም ዕጦት መፍትሔ እንዲያገኝ የተጠየቀበት ነበር፡፡
‹‹እኛ እንደ ሠራተኛ በሚኒስቴር ደረጃ የተወከለ የለንም፡፡ ሁልጊዜ የሥራና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ እየተባለ የሚጠቀሰው ቀርቶ ቢያንስ ሠራተኛውን የሚወክል ሚኒስቴር ይኑረን›› ተብሏል፡፡
‹‹እኛ የአገራችን የፖለቲካ ጉዳይ አያገባንም ወይ?›› የሚለው ጥያቄ የዛሬ ሁለት ዓመትም ይሄ ጉዳይ መነሳቱን ያስታወሱት አስተያየት ሰጪው ለምንድነው? ሕገ ደንባችንን የማናሻሽለው እንደ እንግሊዝ ሠራተኛውን የሚወክል የሌበር ፓርቲ አያስፈልገንም ወይ? በእኛስ ጉዳይ ራሳችን መወሰን እንድንችል ሠራተኛው የራሱ ፓርቲ ሊኖረው ይገባል፤›› የሚል ጥያቄም ቀርቧል፡፡
የሌበር ፓርቲ ጉዳይ ‹‹እኔ በቀላሉ የምመልሰው ጉዳይ አይደለም ያሉት አቶ ካሳሁን፣ በሕገ ደንባችን መሠረት ፓርቲ ማቋቋም አንችልም፤›› ብለዋል፡፡
ነገር ግን በሥራ ላይ ያሉና የተቋቋሙ ፓርቲዎችን ማገዝ እንደሚቻል ጠቅሰዋል፡፡ ለጊዜው የአገራችን ፖለቲካ ምን ላይ እንደተመሠረተ ፓርቲ ይታወቃል፡፡ አይዶሎጂ ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ አይዶሎጂ ላይ ያልተመሠረተ ደግሞ፣ ለእኛ አይጠቅመንም፡፡ እኛ የራሳችንን ፓርቲ እናቋቁም ከተባለ ደግሞ ይህንን ለማድረግ ጥናት ማድረግን ይጠይቃል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ኢሰማኮ ግን በቀጥታ ፓርቲ ማቋቋም እንደማይችል በመግለጽ ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ይህ ማለት ግን ሠራተኛውን የሚደግፍ ካለ ይደግፋል፡፡ እስካሁን ባለው አሠራር ግን ሠራተኞች ራሳቸው ይጠቅመኛል ያሉትን በግላቸው ይምረጡ የሚል ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ይህንን ጥያቄ ረገብ ማድረግ የሚመረጥ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡