- ሃሎ!
- እንዴት አሉ ክቡር ሚኒስትር።
- ደህና ነኝ።
- ክቡር ሚኒስትር ባለፈው ወደ አዲስ አበባ የመጣሁ ጊዜ በተመለከትኩት ሳላደንቅዎ ማለፌ ፀፅቶኝ ነው የደወልኩት።
- ምን አይተህ ነው?
- እያስገነቡት ያለውን የኮሪደር ልማት።
- ኦ…ዞር ዞር… ብለህ ተመለከትከው?
- መመልከት ብቻ ክቡር ሚኒስትር?!
- እ…?
- አዲስ አበባ መሆኔን ጭምር ነው የተጠራጠርኩት።
- የትኛውን ከተማ መሰለችህ?
- ኬፕታውን።
- የእኛም ዕቅድ ኬፕታውንን እንድትመስል ማድረግ ነው።
- እንድትመስል?
- አዎ።
- ሆነች እኮ ክቡር?!
- አመሠግናለሁ፣ እናንተም ጋ ለውጥ አለ፣ እናም ይኼ ጥሩ ጅምር ነው።
- ምኑ ክቡር ሚኒስትር?
- እንዲህ የሚደነቀውን ማድነቅ መጀመራችሁ ጥሩ ነው ማለቴ ነው፣ ግን…
- ግን ምን ክቡር ሚኒስትር?
- እንዲሁ ስገምት የደወልከው ለዚህ ጉዳይ ብቻ አልመሰለኝም፣ ልክ ነኝ?
- በእርግጥ የደወልኩት ለሌላ ጉዳይ ነው።
- ምነው? ሰሞኑን ተገናኝተን ከገመገምን በኋላ የተፈጠረ ነገር አለ እንዴ?
- የለም።
- እና ምን ገጠመህ?
- ሰሞኑን ተነጋግረን የተግባባንበትን ጉዳይ በተመለከተ ለመጠየቅ ነው አደዋወሌ።
- የትኛው ጉዳይ?
- ዘነጉት እንዴ?
- ምን ነበር?
- የፓርቲያችን ሕጋዊ ሰውነትን በተመለከተ ተወያይተን ተግባብተን ነበር።
- ኦ… ዘንግቼው ነው፣ ልክ ነህ።
- እና በዚያ ጉዳይ ላይ ፈቃድዎን ለመጠየቅ ነበር።
- ምን?
- ያስታውሱ ከሆነ የፓርቲያችን ሕጋዊ ሰውነት የተሰረዘው ግንቦት 7 ቀን ነበር።
- እኔ እንጃ ትዝ አይለኝም።
- ለነገሩ ሥራ ይበዛብዎታል ሊያስታውሱት አይችሉም።
- እሺ? ታዲያ የተሰረዘበት ቀን ግንቦት 7 መሆኑ የተለየ ትርጉም አለው እንዴ?
- አዎ፣ ለእኛ መጥፎ ትርጉም አለው።
- እና አሁን ምን እንዲደረግ ነው የፈለግከው?
- ትዕዛዝ እንዲሰጡልኝ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- የምን ትዕዛዝ?
- ሕጋዊ ሰውነታችን በታሪካዊ ቀናችን እንዲመለስልን።
- ታሪካዊ ቀናችን ነው ያልከው?
- አዎ ክቡር ሚኒስትር።
- መቼ ነው።
- የካቲት 11።
- ጥሩ፣ ከቻላችሁ በዚህ ታሪካዊ ቀን አንድ ላይ ሆናችሁ…
- እ… ክቡር ሚኒስትር?
- ጉባዔ አድርጉ!
[ክቡር ሚኒስትሩ በፓርቲያቸው የሕዝብ ድጋፍ ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ የዳሰሳ ጥናት እንዲያካሂድ የተዋቀረው ኮሚቴ ሰብሳቢ ባቀረቡት ውጤት ላይ እየተወያዩ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር የተደረገው የዳሰሳ ጥናት የፓርቲው የሕዝብ ድጋፍ በፍጥነት እየቀነሰ መምጣቱን የሚያሳይ ነው፣ በተለይ…
- በተለይ በከፍተኛ የኑሮ ውድነትና የሕግ አስከባሪ አካላት በሚወስዱት ዕርምጃ ማኅበረሰባችን ተማሯል።
- እኔ በዚህ ድምዳሜ አልስማማም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እርስዎ ባይስማሙም የተደረገው የዳሰሳ ጥናት የሚያሳየው እንደዚያ ነው።
- እኔ አልስማም፣ ለጥናቱ መመዘኛ የሆነው መረጃ ትክክለኛ አይመስለኝም።
- እንዴት?
- የሕዝብን ድጋፍ ለመመዘን ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎች የተወሰዱ አይመስለኝም፣ ጠቃሚ የሚባሉት መመዘኛዎች ተወስደው ቢሆን ኖሮ እዚህ ድምዳሜ ላይ ሊደረስ አይቻልም።
- ተገቢና ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎች ተወስደው የተከናወነ ጥናት መሆኑ እኮ በሪፖርቱ ተቀምጧል ክቡር ሚኒስትር?
- እኔ አይመስለኝም፣ እንዳንሳሳት እሠጋለሁ።
- ክቡር ሚኒስትር ወጣቱም፣ አርሶ አደሩም፣ አርብቶ አደሩም አኩርፎናል እኮ፣ በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ማኩረፍ ብቻ ሳይሆን ነፍጥ አንግቦ እየተጋጨን መሆኑ እየታወቀ እንዴት ስህተት ሊሆን ይችላል?
- ስህተት አለበት አልኩህ እኮ።
- እንዴት?
- ምክንያቱም የሕዝብ ድጋፍ ያለበትን ደረጃ ለመለካት ሁነኛ ናቸው የሚባሉት መመዘኛዎች ጥቅም ላይ አልዋሉም።
- ኩቡር ሚኒስትር፣ እርስዎ ሁነኛ የሚሏቸው መመዘኛዎች ምንድናቸው?
- ለምሳሌ አንዱ የኮሪደር ልማት ነው፣ ሌላኛው ማዕድ ማጋራት ነው።
- እ…?
- አዎ፣ የማዕድ ማጋራት ጋብዘን አልመጣም ያለ ነዋሪ አለ?
- የሚበላው የተቸገረ ሰው ግብዣ ቀርቦለት አንዴት ይቀራል ክቡር ሚኒስትር?
- ተው ተው፣ ይኼ ብቻ አይደለም።
- እሺ ሌላው መመዘኛ ምንድነው?
- የመደመር መጽሐፍ አልገዛም ያለ የማኅበረሰብ ክፍል አለ?
- እሱን በመመዘኛነት አልተጠቀምንበትም።
- ችግኝ ትክሉ ስንል የቀረ ሰው አለ? የሌማት ትሩፋትንስ በመመዘኛነት ተጠቅማችኋል?
- አልተጠቀምንም?
- ታዲያ ይኼ ጥናት ነው?