የአገራችን ኢትዮጵያ ከ65 በመቶ በላይ የሚሆን ኢኮኖሚ የሚንቀሳቀሰው በአዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ የአገራችን ባንኮች በየዓመቱ ለብድር ከሚያውሉት ገንዘብ ውስጥ ከ70 በመቶ ያላነሰው ከዚሁ አዲስ አበባ የሚገኙ ተበዳሪዎች የሚሰጥ ነው፡፡ በአዲስ አበባን ለብቻዋ ነጥለን ስናይ ደግሞ የበዛው የገንዘብ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት ሥራ መርካቶ ነው፡፡ መርካቶ ከጥቃቅን ቸርቻሪዎች ጀምሮ ትልልቅ አስመጪዎችና የጅምላ አከፋፋዮችን በመያዝ ሚሊዮንና ቢሊዮን ብሮች በየዕለቱ የሚያንቀሳቅሱባት ነች፡፡ በሕገወጥ መንገድ የሚገቡ ምርቶች የሚቸበችቡባትም በመሆንም ትታወቃለች፡፡ ሕገወጥና ሕግ አክባሪ ነጋዴዎች ተደበላልቀው የሚሸቅጡባትም ሆና ለዓመታት መቆየቷን እንገነዘባለን፡፡
የመርካቶ ትልቅ የኢኮኖሚ ማዕከል ለመሆኑ ብዙ መገለጫዎች አሉት፡፡ የባንክ ቅርንጫፎች ከሌላው በተለየ በመርካቶና አካባቢዋ ሥራ የሚበዛባቸው ዋናው ምክንያት በመርካቶ የሚገላበጠው የገንዘብ መጠንና የንግድ እንቅሰስቃሴ ሳይቋረጥ የሚካሄድበት በመሆኑ ጭምር ነው፡፡ መርካቶ በብዙ ምክንያቶች የአገሪቱ የንግድ መናኸሪያ ብቻ ሳትሆን የኢኮኖሚ የስበት ማዕከልም ነች፡፡ በመሆኑም የመርካቶ የንግድ እንቅስቃሴ መስተጓጎል በሁሉም የአዲስ አበባ መውጫ ወደ ሁሉም ክልሎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ መርካቶን የግብይት ማዕከል በማድረግ ከየአቅጣጫው የሚገቡ ምርቶች የገበያ እንቅስቃሴ ከማቀዝቀዝ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ጭርታም ይፈጥራል፡፡
በክልሎችም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያሉ የንግድ መደብሮች በየአካባቢ ላሉ ነዋሪዎች በችርቻሮ የሚያቀርቡት ምርት መነሻው ከመሆኑ አንፃር የመርካቶ እንቅስቃሴ በምንም ሁኔታ ቢስተጓጎል ንዝረቱ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ባሉ ገበያዎች እንዲሰማ ያደርጋል፡፡ በዚያ አካባቢ የሚፈጠር ችግር ቀላል የማይባል ተፅዕኖ ማድረሱ አይቀርም፡፡ ከሰሞኑ በተፈጠረ ውዥንብርና አንዳንድ መደብሮች መዘጋት ምክንያት የአንዳንድ ምርቶች ዋጋ ያልተጠበቀ ጭማሪ ማሳየታቸው ብቻ ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ መርካቶ መረበሽ የለበትም፡፡
ከሰሞኑ ከግብር ደረሰኝ ጋር በተያያዘ እየተሰማ ያለው ንቅናቄ በአግባቡ ተይዞ መላ ካልተበጀለት ይብዛም ይነስም ኢኮኖሚው ላይም ሆነ በአጠቃላይ የቢዝነስ እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደደሩ አይቀርም፡፡ በዚህ ተጎጂዎች ቢኖሩም በተለይ የሸማቹ ጉዳት ጎልቶ ሊወጣ ይችላል፡፡ መርካቶን ማዕከል አድርገው ወደ ገበያ የሚገቡ ምርቶች እንዳይገቡ በማድረግ ንዳንድ ምርቶች ላይም እጥረት ሊፈጠር የሚችልበት ዕድል ሊኖርም ይችላል፡፡ ስለዚህ በመርካቶ አካባቢ ተፈጠረ የተባለው ችግር በአግባቡና በዘዴ ሊፈታ ይገባል፡፡ ይህ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ማዕከል የሚባለው ገበያ በተረጋጋና ሕጋዊ በሆነ መንገድ የሚሠራበት ሥፍራ ሊሆን እንደሚገባውም መተማመን ያስፈልጋል፡፡ ከሰሞኑ የተፈጠረውን ችግር የአንድ ወገን ችግር ብቻ አድርጎ መውሰድ እንደማይገባም መታወቅ አለበት፡፡
በሌላ በኩልም ከልማዳዊ አሠራር ወጥቶ ጊዜው በሚጠይቀው አግባብ መሥራትን ማዳበር አስፈላጊነት ላይ ጥያቄ ሊነሳ አይገባውም፡፡ በአፍሪካ ትልቁ ገበያ እያልን የምንጠራው ሥፍራ የበለጠ ልንኮራበት የምንችለው በሕጋዊ መንገድ ግብይት የሚካሄድበት ሲሆን ጭምር መሆኑን በመረዳት የቢዝነስ ሥራውን ዘመናዊና ሕጋዊ ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡
ሁሌም በዘልማድ የሚነገድባትና በጥቂት ደላሎች የምትዘወር መሆን እንደሌለባትም ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ከዘመናዊነት መለኪያዎች መካከል አንዱና ዋነኛው ሕግና ሥርዓቱን ጠብቆ መነገድ ነው፡፡ ይህ በደረሰኝ ገዝቶ በደረሰኝ መገበያየትን ይጨምራል፡፡ ከአየር በአየር ንግድ እጅን መሰብሰብ ግድ የሚልበት ጊዜ ላይ መድረሱን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
ከሰሞኑ ተከሰተ የተባለው ችግር አንዱ መነሻ ከተለመደ አሠራር ካለመላቀቅ ጋር የተያያዘ ነው ቢባል ከእውነት መራቅ አይሆንም፡፡ በእርግጥ በዚህ አካባቢ ያሉ አንዳንድ ነጋዴዎች (ሁሉም አይደሉም) ከሰሞኑ መደብሮቻቸውን የዘጉበት ምክንያትም በትክክል ደረሰኝ ለመቁረት እንቢ በማለታቸው ከሆነ ትክክል አይደለም፡፡ በደረሰኝ ተገበያዩ ማለት ስህተት ሊሆን አይችልም፡፡ ዘለዓለም አየር በአየር እየተነገደ አይኖርም፡፡ ብልሹ የሕግ አስከባሪዎች ጉቦ እየሰጡ መቀጠልም አግባብ አይሆንም፡፡ ሕጋዊ ነጋዴዎች ከሆኑ ለሚገዟውም ሆነ ለሚሸጡትም ዕቃ ደረሰኝ መጠቀም ግድ ነው፡፡ ደረሰኝ በመስጠት ሊያጡት የሚችሉት ነገር አለ ተብሎ አይታሰብም፡፡ እስከዛሬ ሲሠሩ የነበረው ደረሰኝ ሳይቆርጡ ወይም ለተወሰነው ደረሰኝ እየሰጡ ለተወሰነው ያለ ደረሰኝ የሚሠሩ ከሆነም ይህም ስህተት እንደነበር መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ችግር የነጋዴዎች ብቻ ሳይሆን የመንግሥትም ጭምር ነው የምንልበት ብዙ ምሳሌዎች መቅረብ ስለሚችሉ ነው፡፡ መንግሥት የሚመድባቸው የሕግ አስከባሪዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ባለመቻላቸው የተፈጠረ ጭምር መሆኑ አይካድም፡፡ ዛሬ ደረሰኝ ለመቁረጥ የተቸገሩ አንዳንድ ነጋዴዎች ዕቃውን መርካቶ ያስገቡት በሕገወጥ ተቆጣጣሪዎች ትብብር ጭምር በመሆኑ ተጠያቄዎቹ በሁለቱም ወገን የሕገወጥ ተግባሩ ተሳታፊዎች ናቸው፡ መፍትሔውም በሁለቱም ወገኖች ያሉ ሕገወጦች በእኩል በመዳኘት አለበት፡፡
ያለ ደረሰኝ ሲደረግ የነበረ ግብይት እየታየ እንዳልታየ ሆኖ ለዘመናት መቆየቱም ዛሬ በአንዴ እናስተካክለው ሲባል እንቅፋት የተፈጠረበቱ አንዱ ምክንያት በሙስና የተጨመላለቀ አካላት በፈጠሩት ስህተት ጭምር መሆኑን በማመን፣ ለመፍትሔም መንግሥት በራሱ ቤት ውስጥ ያለውን ችግር በማጥራት ሊጀምር ይገባል፡፡
መርካቶ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የንግድ ሥፍራዎች ያለ ደረሰኝ የሚደረጉ ግብይቶች ለመበራከታቸው አንዱ ምክንያት የተቆጣጣሪ አካላት ሠራተኞች ሥራቸውን በአግባቡ ባለመሥራታቸው ጭምር የሚፈጠር ነው፡፡ ሕገወጥ ነጋዴዎቹም ትክክለኛ ገቢና ወጪውን ለመሸሸግ ሲሉ ብልሹ ተቆጣጣሪዎችን በመመርኮዝ የሚሠሩ እንደነበሩ ታውቆ አሁን ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ የሚፈለግበት መንገድ ይህንኑ ታሰቢ ማድረግ አለበት፡፡
ጉምሩክ የሚያውቀውም ሆነ የማያውቃቸው ዕቃዎች መርካቶ የሚገቡት ሕጋዊ የሆኑ መሥፈርቶችን አሟልተው ካልሆነ በዚህ ሒደት ኪሳቸውን እያሳበጡ ያሉትን ከሲስተሙ ማስወጣት ያስፈልጋል፡፡ ዛሬም እንደ ችግር የምንሰማውና የሚነግረን ደረሰኝ ለመቆረጥ የተቸገሩ ነጋዴዎቹ እንደ ምክንያትነት ያሉት አስመጪዎችና አምራቾች ደረሰኝ አይሰጠንም የሚል ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያለ ምክንያት እየቀረቡ ያሉ ነጋዴዎች እስከዛሬ ሲሠሩ የነበሩት በዚህ መንገድ ከሆነ ይህንኑ ለማስተካከል የተሰጠውን ዕድል በመጠቀም ወደ መስመር መግባት አለባቸው፡፡ ከስሜታዊነት ወጥተን ድርጊቱን ከመረመርን ደረሰኝ የሌለውን ምርት መሸጥና ማከፋፈል ወንጀል ነው፣ እንዲህ ባለ መንገድ የሚሸጥ ዕቃስ እንዴት ሒሳቡን ማወራረድ ይቻላል?
በሌላ በኩል በተለይ በዚህ ወቅት ልማዳዊ የግብይት ሥርዓትን ማዘመን የሚያስፈልግበት ዋናው ምክንያት፣ ዛሬ የመርካቶ ነጋዴዎች የሚሠሩትን ተመሳሳይ ሥራ የሚሠሩ የውጭ ኩባንያዎች የሚገቡ መሆኑን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለተመሳሳይ ሥራ የሚገባው የውጭ ኩባንያዎችም ደረሰኝ ቁረጥ አትቁረጥ ከሚል አላስፈላጊ ንትርግ ወጥተው ለውድድር መዘጋጀት አለባቸው፡፡
በውድድር ላይ የተመሠረተ ነፃ ገበያ ለመፍጠርና እንዲሁም ጥሩ ተወዳዳሪ ሆኖ አሸንፎ ለመውጣት ደግሞ ከዘልማዳዊ አሠራር መውጣትን ስለሚጠይቅ ሕጋዊ መስመሮችን መከተል የሚጠቅመው ለራሳቸው ጭምር ነው፡፡
ቀድሞም ቢሆን የተበላሸን ዛሬ ለማስተካከል ሲፈለግ ደግሞ መንግሥትም ሱሪ በአንገት ከማለት ይልቅ ስህተቱ እንዳይደገም የእስካሁኑን በመግባት ፈትቶ እንደ አዲስ የሚሠራበት አካሄድ ቢከተል ደረሰኝ መስጠትና መቀበል የሚፀየፉ ሕገወጦችን በቀላሉ መለየት ሊያስችል ይችላልና ለመፍትሔው የተለያዩ አማራጮ ይታዩ፡፡ ሥራው በጊዜያዊነት እሳት ማጥፋት ብቻ ሳይሆን ለዘለቄታው መፍትሔ እንዲሆን ታሳቢ መደረግ አለበት፡፡
ከዚህ ባሻገር ግን ይህንን አሠራር ከለላ በማድረግ ነጋዴዎችን ለማጥቃት ታስቦ ከሆነ ይህ በምንም ሁኔታ ተቀባይነት የለውም፡፡ በደረሰኝ መገበያየት ሕግ በመሆኑ ይህ መተግበር አለበት ከተባለ፣ ሕግ ማስከበር ያለበት በሕጉ አግባብ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን የከረመ ሕገወጥነት በአንድ ጀምበር አስተካክላለሁ ከሚል ይልቅ፣ ከንግዱ ኅበረተሰብ ጋር ቁጭ ብሎ መምከር ያስፈልጋል፡፡ ከሲህ አንፃር ከሰሞኑ አንዳንድ የውይይት መድረኮች ተዘጋጅተው ሐሳብ ለመቀያየር የተደረገው ሙከራ ጥሩ ቢሆንም፣ ከችግሩ ጥልቀት አንፃር በእነዚህ መድረኮች ላይ ብቻ በተንሸራሸሩ ሐሳቦች ዘላቂ መፍትሔ አይመጣም፡፡ መቼም ቢሆን ያለ ደረሰኝ መገበያየት ሕገወጥ መሆኑ ሀቅ ቢሆንም ዛሬ ደረሰኝ ላለመቁረጥ የሚሰጡ አንዳንድ ምክንያቶች በተጨባጭ ትክክል የሚሆኑበት አግባብ እንዳለ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ወደ መርካቶ የሚገቡ ዕቃዎች በትክክል ሕጋዊነትን ጠብቀው ነው ወይ? ከተባለ መልሱ አይደለም ነው፡፡ ችግሩ መቆጣጠር እየተቻለ ባለመቆጣጠር የተፈጠረ መሆኑን በማመን እዚህ አካባቢ ብዙ ሥራ እንደሚያስፈልገው መገንዘብ ይገባል፡፡ ስለዚህ በደረሰኝ ላለመገበያየት ፍላጎት የታጣበት ምክንያት በሚገባ ተፈትሾ፣ ከዚህ በኋላ ምን ዓይነት መፍትሔ ይደረግ የሚለው ላይ ራሳቸው ነጋዴዎች ሐሳብ እንዲሰጡበት በማድረግ ዘላቂ መፍትሔ የሚገኝበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል፡፡
ቀድሞ የተበላሸውን ነገር ለዘለቄታ ለማስተካከል የተሻለው አማራጭ የቱ ነው? ብሎ በጥንቃቄ በመመርመር የሚያደርግም ዕርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ የእስካሁኑ በእጅ ያለ ዕቃ እንዴት ይወራረድ ለሚለው መልስ ሰጥቶ ከዚህ በኋላ እንደ አዲስ የሚጀመርበት አሠራርም አዋጭ ከሆነ ይህንኑ ማሰብም ያስፈልጋል፡፡ ችግሩ የነጋዴዎች ብቻ ሳይሆን የአስፈጻሚው አካላት ውስጥ ያለ ብልሹ ተግባር በመሆኑ፣ ሕገወጥ አሠራሮችን ለመከላከል ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የከረሙ ጉዳዮችን ደፍሮ በአዲስ ፋይል እንዲተኩ መሞከርም ለውጤት ሊያበቃ የሚቻልበት ዕድል ይኖራል፡፡
ደረሰኝ መቁረጥ ሕግ ማክበር፣ ያለመቁረጥ ተጠያቂ የሚያደርግ መሆኑን ማንም ባያጣውም ሱቅ እስከ ማዘጋት የተደረሰበት ምክንያት የብዙኃኑ ፍላጎት ይሆናል ብሎ ለማሰብ ይከብዳልና ችግሮችን በመነጋገር መፍታት እንጂ አድማ በመልካም አይታይም፡፡ ምክንያቱም ይህ ዓይነቱ ነገር የብዙዎች ስለማይሆን ነው፡፡ ነገር ግን ሕገወጦች አጋጣሚውን በመጠቀም በሕገወጥነታቸውን ለመቀጠል ሁኔታውን ሊያጋግሉ ስለሚችሉ መንግሥትም ሆነ ነጋዴው መደማመጥ ግድ ይላቸዋል፡፡
የመርካቶን ገበያ ማስተጓጉል ኢኮኖሚውን የሚጎዳ በመሆኑ ሕገወጦች በሚፈጥሩት ውዥንብር የመርካቶን ገበያ መረበሽ አግባብ አይሆንም፡፡ መንግሥትም ቢሆን ሕግ ማስከበር ያለበት ቢሆንም፣ በሕግ የተቀመጠውን ድንጋጌ ለመተግበርና ዘላቂ ለማድረግ የነጋዴውን ድምፅ ያዳምጥ፡፡
ስለዚህ በመርካቶ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ በኢኮኖሚው ውስጥ የግብይት ሥርዓቱ ፈር ይያዝ፡፡ ሸማቹም ደረሰኝ ይሰጠኝ ይበል፡፡ ለዘለቄታውም የሚጠቅመው በሕግና በአግባቡ መነገድና ማገልገል ነው፡፡ መንግሥትም ቢሆን መገዳደር የሚችለው ሕግ አክብረንን ስንሠራ መሆኑንም ማወቅ ተገቢ ይሆናል፡፡ ‹‹በዝሆኖች ጡብ የሚጎዳው ሳሩ ነው›› እንደሚባለው ሁሉ በዚህ መሃል አንዱና ዋና ተጎጂ እየሆነ ያለው ሸማች ነውና ለእሱም ይታሰብ፡፡ አሁን የተሸከመው የዋጋ ንረት ሳያንስ ሌላ የዋጋ ንረት ምክንያት ስለማይፈልግ ነጋዴውም ሕግ ያክብር በደረሰኝ ይግዛ በደረሰኝ ይሽጥ፡፡ መንግሥትም ለሕገወጥ ተግባራት የሚተጉ ሙሰኛና ሌቦች ሠራተኞችን ነቅሶ በማውጣት ሚዛናዊ ዳኝነት ይስጥ፡፡ ሕጋዊ የግብይት ሥርዓት ያሥፍን፡፡ በተለይ በመርካቶ!.