- የስድስት ቀናት ሥልጠና ሲጠናቀቅ የመቋቋሚያ ገንዘብ ለሠልጣኞች እንደሚሰጥ ተነግሯል
- የሥልጠና ማዕከላቱ በጦርነቱ የወደሙ የሰሜን ዕዝ ማዕከላትን በማደስና በማደራጀት መቋቋማቸው ታውቋል
ከዓለም አቀፍ አጋር አካላት በተሰባሰበ 60 ሚሊዮን ዶላርና ከፌዴራል መንግሥት በተገኘ አንድ ቢሊዮን ብር ድጋፍ 75,000 የትግራይ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ በማስፈታት ከሠራዊት ለማሰናበትና ጊዜያዊ መልሶ ማቋቋሚያ የሚሆኑ ሦስት ፕሮጀክቶች ይፋዊ ትግበራ ሲጀመር፣ ሥልጠናቸውን ላጠናቀቁ ገንዘብ በባንክ ሒሳብ ቁጥራቸው ገቢ እንደሚደረግላቸው ታወቀ።
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ኅዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም. በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ በሚገኝ ማዕከል የተጀመረውን የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ በተመለከተ፣ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ዝርዝር መረጃዎችን ይፋ አድርጓል።
ኮሚሽነሩ አቶ ተመስገን ጥላሁን በሰጡት ማብራሪያ መሠረት የማዕከላት ልየታ ሥራ በተከናወነበት ወቅት ከቀረቡ አማራጮች መካከል ለሠራዊት ብተና (Demobilization)፣ ትጥቅ ማስፈታት (Disarmament) እና መልሶ ከማኅበረሰቡ ጋር መቀላቀል (Reintegration) ሥራዎች ለማስጀመር የሚያስችሉ ማዕከላትን አዘጋጅቶ የቀድሞ ተዋጊዎችን በማሰባሰብና አሠልጥኖ ወደ ማኅበረሰቡ በጊዜያዊነት በመቀላቀል የማቋቋም ሥራዎችን ማስቀጠል የሚለው አካሄድ በኮሚሽኑ መመረጡን ገልጸዋል።
በዚህም በትግራይ ክልል በመጀመሪያ አሥር የሚሆኑ ቦታዎችን ለሠራዊት ስንብት ሥልጠናዎች የሚሆኑ ማዕከላት በሚል መለየታቸውን፣ በሒደትም ብዛታቸውን ወደ አምስት በመቀነስ አሁን ሦስት ማዕከላትን በማስቀደም ሥራዎች እንዲከናወኑ ኮሚሽኑ መወሰኑም ታውቋል።
ሦስቱ ቦታዎችም በመቀሌ፣ በዕዳጋ ሐሙስና በዓድዋ የሚገኙ መሆናቸውንና በቅድሚያ በመቀሌ ማዕከል በመጀመር፣ በቅደም ተከተላቸው መሠረት ሥራውን የማስፋት ዕቅድ መያዙንና አስፈላጊ ከሆነም ሌሎች ሁለት ማዕከላት እንደሚጨመሩ አቶ ተመስገን ገልጸዋል።
‹‹እነዚህ ማዕከላት ቀድሞ የሰሜን ዕዝ ይጠቀምባቸው የነበሩ ናቸው። በጦርነቱ የተጎዱ ስለሆኑ የማስተካከልና የመጠገን ሥራ ሰፊ ጊዜ ወስዷል። አሁን የመቀሌና የዕዳጋ ሐሙስ ማዕከላት ጥገናቸው አልቆ ለቅበላ ዝግጁ መሆናቸውን ስላረጋገጥን ነው ሥራውን ለመጀመር የተነሳነው፤›› ብለዋል።
ኮሚሽነሩ በአጠቃላይ ትግራይን ጨምሮ በስድስት ክልሎች የሚገኙና ትግበራ ሲጀመር በምዝገባ ወቅት ሙሉ በሙሉ ቁጥራቸው የሚረጋገጥ 371,971 የቀድሞ ተዋጊዎችን በኮሚሽኑ መለያታቸውን፣ በአጠቃላይ የተሃድሶ ትግበራው በሦስት ምዕራፍ እንደሚከወን አብራርተዋል።
በዚህም መሠረት የፕሮግራሙ ትግበራ በመጀመሪያው ዙር 75,000 የቀድሞ ተዋጊዎች ከትግራይ ክልል ብቻ ተጠቃሚ እንደሚሆኑና ሴቶች፣ ዕድሜያቸው የገፉና የአካል ጉዳት ያለባቸው ቅድሚያ ትኩረት እንደሚያገኙ ተጠቅሷል።
በሁለተኛ ዙር 100,000 የቀድሞ ተዋጊዎች እንደሚካተቱና ከእነዚህም አብዛኛው ከትግራይ ክልል ሆነው፣ ነገር ግን በኮሚሽኑ አሠራር መሠረት ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተው ወደ ሰላማዊ ሥርዓት የገቡ የቀድሞ ተዋጊዎችና ድርጅቶች ያሉባቸው ክልሎች እንደሚካተቱም ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ በሦስተኛ ዙር 150,000፣ እንዲሁም በመጨረሻው ምዕራፍ 50,000 የቀድሞ ተዋጊዎች በፕሮግራሙ እንደሚካተቱ ተነግሯል።
በስድስቱም ክልሎች አጠቃላይ ትግበራውን ለማከናወን ከ18 ወራት እስከ ሁለት ዓመታት ሊፈጅ እንደሚችል በዕቅድ መያዙ የተገለጸ ሲሆን፣ የመጀመሪያውን ዙር ትግበራ በትግራይ ለማጠናቀቅ የአራት ወራት የአፈጻጸም የጊዜ ገደብ እንደተቀመጠለት ታውቋል፡፡
ከበጀት አንፃር ለአጠቃላይ የፕሮግራሙ ትግበራ 761,490,353 ዶላር እንደሚያስፈልግ የገለጹት አቶ ተመስገን ሠራዊት የመበተን፣ የሥልጠናና በጊዜያዊነት ወደ ማኅበረሰብ የመቀላቀል ሥራዎች ብቻ 501 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመዋል።
በመጀመሪያ ዙር በትግራይ ክልል ላለው ትግበራ ከፌዴራል መንግሥት በሐምሌ 2016 ዓ.ም. አንድ ቢሊዮን ብር በጀት መመደቡን አሳውቀዋል።
አቶ ተመስገን፣ ‹‹ይህ በጀት ባይለቀቅልን ኖሮ ዛሬ እዚህ መድረስ እንደማንችል መታወቅ ይኖርበታል፤›› ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከተለያዩ አገሮች 60 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ መገኘቱን ገልጸው፣ ‹‹ይህ የመጀመሪያውን ዙር በቀጣይ አራት ወራት ውስጥ ለማስፈጸም በቂ ነው፤›› ብለዋል።
ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ከረቡዕ ኅዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ መቀሌ በሚገኘው ማዕከል 320 የቀድሞ ተዋጊዎች ትጥቅ በማስረከብ ወደ ሥልጠና መግባታቸውን አሳውቋል።
እንደ ኮሚሽኑ መረጃ ከረቡዕ ከሰዓት እስከ ሐሙስ ጠዋት ድረስ የመጀመሪያዎቹ 320 ወደ ካምፕ የሚገቡ የቀድሞ ተዋጊዎች የአፍሪካ ኅብረት የቬሪፊኬሽን ቁጥጥርና ግምገማ አባላት፣ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ተወካዮችና የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኃላፊዎችና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተወካዮች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ለመከላከያ ሚኒስቴር ተወካዮች ትጥቅ የማስረከብ ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል።
ትጥቅ የማስፈታት ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ ከሐሙስ ከሰዓት ጀምሮና ዓርብ ሙሉ ቀን የቀድሞ ታጋዮችን ወደ ሥልጠና ማዕከል ማስገባት፣ አስፈላጊውን የቅበላ ኦረንቴሽን በመስጠት ለስድስት ቀናት ቆይታ የሚያስፈልጓቸውን ግብዓቶች እንደሚሰጣቸው ተገልጿል።
ከዚህ በማስከተልም ኮሚሽኑ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) በጋራ በመሆን ባበለፀገው ሶፍትዌር ፎቶግራፋቸው ጭምር የተካተተበት 29 ወሳኝ ዝርዝር ጥያቄዎችን መመለስ ያስችላል ባሉት መንገድ ምዝገባ እንደሚያካሂዱ፣ የምዝገባ ሒደቱ ሲጠናቀቅ ‹የቀድሞ ተዋጊ› መሆናቸውን የሚገልጽ መታወቂያ እንደሚሰጣቸውም ተገልጿል።
አቶ ተመስገን፣ ‹‹ይህ ምዝገባ ከተጠናቀቀ በኋላ ጎን ለጎን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ቀድመን በገባነው ስምምነት መሠረት የንግድ ባንክ ሒሳብ እንዲከፈትላቸው ይደረጋል። ወደ ቤታቸው ሲሄዱ የምንሰጣቸውን ጥቂት የማቋቋሚያ ገንዘብ በቀጥታ ወደ አካውንታቸው ማስገባት ስለሚኖርብን ማለት ነው፤›› ብለዋል።
የገንዘብ መጠኑን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በመጀመሪያው ዙር የተካተቱ የቀድሞ ታጋዮች 200,000 ብር እንደሚከፈል እንደተነገራቸው ገልጸዋል።
ነገር ግን ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የኮሚሽኑ ኃላፊ፣ ‹‹የተባለው ሐሰት ነው። የምንከፍለው ገንዘብ አለ ግን መጠኑ የሚለያይ፣ ለሕዝብ ይፋ የማናደርገውና በሚስጥር የሚያዝ ነው፤›› ብለዋል።
ከዚህ በኋላ የጤና እንዲሁም የጉዳት ሁኔታ በመለየት፣ የሳይኮ ሶሻልና የተሃድሶ ሥልጠናዎች በመስጠት ወደ ማኅበረሰቡ በጊዜያዊነት የመቀላቀል ሥራ እንደሚከናወን ተገልጿል።