- የቀረበው ጥቆማ ተጨባጭ ከሆነ ዕርምጃ እንደሚወሰድ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስታውቋል
ሦስት የደቡብ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ከክልል የጤና ሳይንስ ኮሌጆች የትምህርት ዕድል ተሰጥቷቸው የሚማሩ መምህራንን ከትምህርት ገበታቸው ማገድ፣ በገንዘብ መደራደር፣ እንዲሁም መምህራኑ ትምህርታቸውን የጨረሱበትን ማስረጃ ባለመስጠት ሕገወጥ ድርጊት ላይ መሰማራታቸው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥቆማ ቀረበ፡፡
ይህ የተገለጸው ባለፈው ሳምንት ስድስተኛ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሰባተኛ መደበኛ ስብሰባ፣ የጤና ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ከምክር ቤት አባላት ለቀረባለቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ ነው፡፡
አዳነ አደቶ (ዶ/ር) የተባሉ የምክር ቤት አባል ለጤና ሚኒስትሯ መቅደስ ዳባ (ዶ/ር) ባቀረቡበት ጥያቄ በሐዋሳ፣ በወላይታ ሶዶና በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ከክልል ጤና ሳይንስ ኮሌጆች የትምህርት ዕድል አግኝተው የሚማሩ መምህራን ላይ ሕገወጥ ተግባር እየተፈተመባቸው ነው ብለዋል፡፡
ዕድል አግኝተው የሚማሩ መምህራን መንግሥት የዘረጋውን የጤና ፖሊሲ ለማሳካትና ጥራት ያለው የጤና ባለሙያ ለማፍራት ታስቦ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ ሦስቱ ዩኒቨርሲቲዎች ከክልል ጤና ሳይንስ ኮሌጆች የትምህርት ዕድል ተሰጥቷቸው የሚማሩ መምህራንን ከትምህርት ገበታቸው እንዲታገዱ ማድረግ፣ በገንዘብ መደራደርና ሌሎች ሕገወጥ ተግባሮች ላይ መሰማራታቸውን አስረድተዋል፡፡
ድርጊቱ ለጤና ዘርፉ ከፍተኛ የሆነ የመልካም አስተዳደር ችግር ከመሆኑም በላይ፣ የመንግሥትን ሥራ አደናቃፊ መሆኑን በማመን የሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ጉዳዩን እንዲያጣራ አዳነ (ዶ/ር) ጠይቀዋል፡፡
በተለይ መንግሥት የጤና ዘርፉ ዜጎች ምርታማና ውጤታማ እንዲሆኑ ከዚህ ቀደም በሽታን መከላከል መሠረት ተደርጎ የሚሠራበትን የጤና ፖሊሲ በመከለስ፣ በአሁኑ ወቅት በሽታን መከላከልንና አክሞ ማዳንን መሠረት ያደረገ ፖሊሲ እየተከተለ መሆኑን የፓርላማው አባል ተናግረዋል፡፡
ይህ የሚያሳየው መንግሥት ለጤና ዘርፉ ልዩ ትኩረት መስጠቱን የሚያመላክት እንደሆነ የገለጹት የፓርላማ አባሉ፣ መንግሥት የዘረጋውን የጤና ፖሊሲ ለማሳካት ጥራት ያለው የጤና ባለሙያ ማምረት ወሳኝ መሆኑን በማመን የፌዴራልና የክልል ዩኒቨርሲቲዎችና የጤና ሳይንስ ኮሌጆቹ ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ኃላፊ ዓለሙ ታምሶ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ለሪፖርተር እስካሁን በዩኒቨርሲቲው ይህንን ዓይነት ድርጊት ስለመኖሩ መረጃ የለኝም ብለዋል፡፡ ነገር ግን በውስጥ እንዲህ ዓይነት ድርጊት የሚፈጽሙ አካላት ካሉና ለፓርላማው የቀረበው ጥቆማ ተጨባጭ ከሆነ፣ ዩኒቨርሲቲው ድርጊቱን በፈጸሙ ግለሰቦች ላይ በፍጥነት ዕርምጃ እንደሚወስድ አስረድተዋል፡፡
‹‹በተለይ ይህንን ዓይነት ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች ሕገወጥ መሆናቸው ታምኖበት ተጠያቂ እንዲሆኑ ይደረጋል፤›› ያሉት ኃላፊው፣ አንድ መምህር ከክልል ጤና ሳይንስ ኮሌጆች የትምህች ዕድል ተሰጥቶት ትምህርቱን በአግባቡ ከጨረሰ በኋላ የጨረሰበትን የትምህርት ማስረጃ የማያገኝበት ምክንያት የለም ብለዋል፡፡
ሪፖርተር ከፓርላማ አባል የቀረበውን ጥያቄ መሠረት አድርጎ የወላይታ ሶዶና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎችን በስልክ ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡