በጌታነህ አማረ
እንግዲህ ሁሉም ሰው እንደሚያውቀውና ከታሪክ እንደሚሰማው ከሆነ፣ በቀድሞው ጊዜ ኢትዮጵያ ታላቅ አገር እንደነበረችና አሁንም ተመልሳ ታላቅ እንደምትሆን ነው፡፡ ይህ በአብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የታመነበት ሲሆን፣ መቼ ለሚለው ጥያቄ ግን መልስ ማግኘት አልቻለም። በቀደመው ጽሑፌ የኢትዮጵያ ትንሳዔ መቼ ነው ለሚለው ጥያቄ መልስ ዛሬ ነው የሚል ምላሽ እንደሰጠሁ ይታወሳል። ለዚህም የኢትዮጵያ ትንሳዔ ዛሬ ነው ከተባለ የታለ? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። ለዚህ መልስ ሊሆን የሚችለው ትንሳዔው የሚታየው ሲበሰርና ሲከወን ነው የሚል ይሆናል። ለማብሰርና ለመከወን ደግሞ ቅድመ ዝግጅት ያስፈልጋል። ከዚህ ቅድመ ዝግጅት ውስጥም አንዱና ዋነኛው ሰዎችን የማሳመን ሥራ ነው። ለማሳመን ደግሞ ሳይንሳዊ ሆኖ የተቀመረና መረጋገጥ የሚችል መሆን አለበት። ይህን ለማድረግ ደግሞ ሥራ መሥራትን ይጠይቃል፣ ለመሥራት መተጋገዝ ያስፈልጋል።
ሌላው ትንሳዔ ምን ማለትና ምን እንደሚመስል ባለፈው ጽሑፌ ላይ በሰፊው ለማብራራት የሞከርኩ ቢሆንም፣ አሁንም ሰው በቀላሉ እንዲረዳው በቀላል ቋንቋና ምሳሌ ደግሜ ለማስረዳት ልሞክር። በአሁኑ ጊዜ አሜሪካ በዓለም ላይ ታላቅ አገርና የሰው ልጅ ሰብዓዊ መብት የሚከበርባት ብቻ ሳትሆን፣ አልፋ ተርፋ ለሌሎች አገሮች ዕድገት ሰላምና ሰብዓዊ መብት መከበር አበክራ የምትሠራ አገር ናት። ይህች አገር ታላቅ ከመሆኗ የተነሳ፣ እኛ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የተቀረው ዓለም ለመኖርና ለመወዳጀት ምርጫው የሚያደርጋት አገር ናት። አገሪቱ ታላቅና የተከበረች ከመሆኗ የተነሳ ወደ እዚያ አገር ለመሄድ የሚጠየቀው መመዘኛና ክፍያ ከፍተኛ እንደሆነ ሲነገር ይሰማል። ስለዚህ ኢትዮጵያ ትንሳዔዋ ሲበሰርና ሲከወን በተሻለ መንገድ እንደ አሜሪካ ታላቅ አገር ትሆናለች ማለት ነው። ብዙ ሰዎች ዲቪ በመሙላትና በተለያየ መንገድ ለመኖር ምቹ ወደ ሆነችው አሜሪካ ይሄዳሉ። ኢትዮጵያ አንድ ቀን ታላቅ አገርና ለመኖር ምቹ ሆና መኖር ለሚፈልጉ ዲቪ እንደምታስሞላ፣ ዲቪ ሞልተውም ይሁን በሌላ መንገድ የሄዱ ዜጎችም ተመልሰው እንደሚመጡ ተነግሯል። ይህም ዕውን ይሆናል። ኢትዮጵያ ታላቅ ስትሆን ከሌላው ዓለም ለየት ያለች መሆን ያለባት በታላቅነት ውስጥ ትልቅ መልካምነትን ማሳየት በመቻል ይሆናል። ሌላው የኢትዮጵያን ትንሳዔ ለማብሰርና ለመከወን ቁልፍ የሚባለውን ችግር ለማስወገድ ቁልፍ ሥራ መሆን ያለበት ምንድነው የሚለውን ማወቅ ተገቢ ይሆናል።
በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ ቁልፍ ችግሮች ከሚባሉት ውስጥ ቀንደኛና ዋንኞቹ ድህነትና ኋላቀርነት ሲሆኑ፣ ሌላው ደግሞ ብዝኃነትን የማስተናገድ ችግር ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያን ትንሳዔ ለማምጣት እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ ችግሮችን በዋናነት ማስወገድ ነው። ለማስወገድ ደግሞ ከፍተኛ ኃይል ያለው ሐሳብ ያስፈልጋል። ይህ ሐሳብ ድህነትንና ኋላቀርነትን ደርምሶ የሚጥል መሆን አለበት፡፡ ድህነትና ኋላ ቀርነት ከተደረመሰ ብዝኃነትን ማስተናገድ ይቀላል። ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች አገር ናት። ይህ ደግሞ በአንድ በኩል ውበት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ እኩል ለማስተናገድ ችግር ሆኗል። ይህ ሁሉንም ብሔር እኩል ማስተናገድ ያለመቻል ችግር ደግሞ ለብዙ ዘመናት የግጭትና የጦርነት መንስዔ ሆኖ ቀጥሏል። የጦርነትና ግጭት መኖር ደግሞ ድህነትና ኋላቀርነት በስፋት እንዲንሠራፉ አንዱ ምክንያት ሆኗል። ድህነትና ኋላቀርነት በአደባባይ ሕዝቡን በአለንጋ እየገረፈ ይገኛል። ስለዚህ ይህ በአደባባይ ሕዝብን እየገረፈ የሚያሰቃይ ድህነትና ኋላቀርነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መውደም አለበት። በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ይህን ተገንዝበን ትንሳዔውን በጋራ በመሆን ለመቀበልና ለመከወን ዝግጁ መሆን አለብን።
አብዛኛው ሰው ትንሳዔውን ጠብቀን አልመጣም። መጠበቅ ሰልችቶናል፣ ከእንግዲህም በኋላም ይመጣል ብለን አንጠብቅም፣ ተስፋ ቆርጠናል በማለት ሲናገሩ ይሰማል። ይህ ፈጽሞ ስህተት ነው። ትንሳዔው አለ፣ መጥቶ በራችን ላይ ቆሞ እንድንቀበለው እየጠበቀ ነው። ቀረ የምትሉ ሰዎች ከበራችሁ ደጃፍ ወጥታችሁ አይታችሁት ታውቃላችሁ? ለማስገባትስ ሞክራችኋል? ዝግጅትስ አድርጋችሁ ታውቃላችሁ? አሁንስ ዝግጁ ናችሁ? ካልሆናችሁ ተዘጋጁና ተቀበሉት ላይመለስ መጥቷልና። ትንሳዔ ሲባልስ በዋዛና በፈዛዛ ወይም በቀልድ የምናየው ሰዎች አለን። አሁንም ስለትንሳዔው የሚወራውን የሚጠራጠር ሰው ሊኖር ይችላል። ነገር ግን በቅርብ ጊዜ በተግባር የምናየው ይሆናል፡፡
በነገራችን ላይ ስለትንሳዔ ስናወራ መገንዘብ ያለብን ነገር አለ። ይህም ነገር ትንሳዔ መኖሩ እንጂ የምናስነሳውና የምናበስረው እንዲሁም የምንከውነው እኛ መሆናችንን ማወቅ አለብን እንጂ፣ በራሱ ነፍስ ዘርቶ እየተናገረ የሚመጣ አይደለም። ለዚህ ነው ኃላፊነታችንን ሳንወጣ ቀርተን ትንሳዔውን ማየት የተሳነን። ስለዚህ ይህን ዕውን ለማድረግ በሥራ ማሳየት ያስፈልጋል። ሥራውን ለመሥራት ደግሞ ያው ከላይ እንደጠቀስኩት ከፍተኛ ኃይል ያለው ሐሳብ ያስፈልጋል። ይህን ሐሳብ ተግባር ላይ ለማዋል በቅድሚያ በአግባቡ መመርመርና ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
ምንም እንኳን ለመከወን ሐሳቡ መሠረታዊ ቢሆንም፣ ትልቁ ሥራ ግን ወደ ተግባር መቀየሩ ነው። እንደሚባለው አንድን ዓላማ ለማሳካት 20 በመቶ የሚይዘው ሐሳብ ሲሆን፣ 80 በመቶ ደግሞ ወደ ተግባር የመለወጥ ሚናን ይጠይቃል ማለት ነው፡፡ ወደ ተግባር ለመቀየር ወይም 80 በመቶ የሚሆነውን ሥራ ለመሥራት ደግሞ የመላው ሕዝብ ትብብር ታክሎበት አቅምና ችሎታ ሊኖረው የሚችለው መንግሥት ነው። መንግሥት ደግሞ ይህን ሠርቶ ታሪኩን በመቀየርና ሌላ አዲስ ታሪክ በደማቅ ቀለም ለመጻፍ በአንክሮ መከታተልና ለመከወን ፈቃደኛና ዝግጁ መሆን ይጠበቅበታል። የኢትዮጵያን ትንሳዔውን ለመከወን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ለመኖር ከምናደርገው ጥረት ውጪ የተለየና ከባድ ጥረት የማይጠይቅ ብቻ ሳይሆን፣ ለመከወን ምንም ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳት የሌለውና፣ በደስታና በፍቅር ሊሠራ የሚችል ከመሆኑም ባሻገር፣ አነስተኛ ጥረት አድርገን ከፍተኛ ስኬት የምናገኝበት ነው። ወይም ደግሞ ሊሆን የሚችለው ኢኮኖሚያዊ ስብራቶች ተጠግነው ይድናሉ፣ የሥራ አጥነት ችግር ይወገዳል። በዚህም የተነሳ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ድሎች ይመዘገባሉ ማለት ነው።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሰው ልጅ አዕምሯዊ፣ አካላዊና መንፈሳዊ ደኅንነቱ ዳብሮና ተጠብቆ ፍፁም ሰላማዊና ምድረ ገነት የሆነች ኢትዮጵያን መፍጠርና ለሌላውም ዓለም የዚህ ምሳሌ መሆን ነው። እንደሚታወቀው በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያውያን አንድነታችን ጠፍቷል በማለት ሲሠጉና አንድ የሚያደርገንን ሁኔታ ሲናፍቁ ይሰማል፡፡ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያውያንን አንድ ያደረጉ ብዙ ክስተቶች ታይተዋል፡፡ ከእነዚህም ክስተቶች ውስጥ ከቅኝ ግዛት ለመውጣት የተደረገው የዓድዋ ጦርነት፣ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታና ከኢሕአዴግ መንግሥት ለውጥ ማግሥት መጥቶ የነበረው አዲስ ራዕይና ተስፋ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድ አድርገው ያሳዩ ክስተቶች ሆነው አይተናቸዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህ አንድነቶች በነበሩበት ቀጥለው ሲሄዱ አልታዩም፡፡ አሁንም በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የኢኮኖሚ የፖለቲካና የማኅበራዊ ቀውሶች እንዳሉ የሚታመን ሲሆን፣ እነዚህን ቀውሶች ደግሞ ለመፍታት ትንሳዔውን የማምጣቱ ዓላማ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድ የሚያደርግና የሚመጣውም አንድነት ቀጣይነት ያለው ማድረግ በጣም ተገቢነት ያለው ጉዳይ መሆን አለበት፡፡ የኢትዮጵያውያን አንድነት ደግሞ ምን ያህል ኃይል እንዳለው የሚታወቅ በመሆኑ፣ ስለዚህ ጉዳይ መናገር ለቀባሪ የማርዳት ያህል ስለሚሆን በዝምታ ማለፉ የሚሻል ይመስለኛል፡፡
ስለዚህ በዋናነት መንግሥት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ጸሐፍት፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ባለሀብቶች፣ የመንግሥትና የግል ተቋማት፣ እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የኢትዮጵያ ትንሳዔ አይቀሬ መሆኑን ተገንዝበው ድጋፍና ትብብራቸውን ከማሳየታቸው ባለፈ ለታሪክ ይቀመጥ ዘንድ፣ ከአሁኑ ሒደቱን በአግባቡ ለመመዝገብና ለመተረክ ዝግጅት ቢጀምሩ መልካም ይሆናል።
ከዚህ በመቀጠል የኢትዮጵያውያንን አንድነት እስከ መጨረሻው እንደ ድር አስተሳስሮ የሚያዘልቀውን ትንሳዔ አይቀሬነት ለማረጋገጥ የሚጠቅሙና የሚያስረዱ ጽሑፎች በቀጣይ የሚወጡ ሲሆን፣ አንባቢያን በደንብ በመከታተል ሐሳባቸውን ይሰጡ ዘንድ መልካም ይሆናል። ከዚያም የኢትዮጵያ ትንሳዔ መበሰር፣ መከወንና መፈጸም ዕውን ይሆናል ማለት ነው።
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የባንክና የኢኮኖሚ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡